Search

"ከፍ ብለን ካላየን የመንደር እና የሰፈር ጉዳዮች ግዙፍ ይሆኑብናል” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኞ መስከረም 25, 2019 89

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ሀገራዊ ዕይታችንን ከፍ ማድረግ ካልቻልን አናሳ የሆኑ የአካባቢ፣ የሰፈር እና የመንደር ጉዳዮች ግዙፍ ሆነው እንደሚታዩን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት በጠበበ ኩሬ ውስጥ እንደሚዋኝ አሳ አስተሳሰባችን እና ዕይታችን ከዕለት ወደ ዕለት እያነሰ እንዳይሄድ መፍትሔው ጠባቡን አስተሳሰብ በሰፊ ዓለም አቀፋዊ እይታ መተካት ነው።

ሰዎች የሥጋት እና የጠበበ አስተሳሰብ ሰለባ ሳይሆኑ አቅም እና አቋማቸውን አስተካክለው ለታላቅ ዓላማ መዘጋጀት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፉ ሥርዓት ስትቀላቀል ማንነቷን አጥታ እና አናሳ ሆና ሳይሆን፣ ራሷን አግዝፋ ዓለምን የምትለውጥ ሀገር መሆን እንዳለባት ጠቁመዋል።

ዓባይ ንጹሕ ሆኖ ተነሥቶ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ሲቀላቀል ጨዋማ እንደሚሆነው፣ ኢትዮጵያም በዓለም አቀፉ ሥርዓት ውስጥ ተዋሂዳ ማንነቷን ልታጣ እንደማይገባ ተናግረዋል።

ሀገራችን በርካታ እምቅ ሀብቶች እና የዘመናት ሥልጣኔ እያላት ለድህነት የተዳረገችው ባልተቋረጡ ሀገራዊ ተቃርኖዎች ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አንዱ ትውልድ የገነባውን ሌላው የሚያፈርሰው እና ከዜሮ የሚጀምረው አዙሪት ሊቆም እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የመብራት እና የውኃ አገልግሎት ማሟላት፣ የቤት ችግርን መቅረፍ እና ኢንቨስትመንትን ማፋጠን ጠቃሚ መንገዶች እንጂ የመጨረሻ መዳረሻዎች እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና የዜጎቿ ዘላቂ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት አዲስ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ሲገነባ ብቻ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስገንዝበዋል።

ለዚህም ሁሉም ዜጋ ትኩረቱን በትልቁ ሀገራዊ ግብ ላይ በማድረግ በቁርጠኝነት እንዲነሣ ጥሪ አቅርበዋል።

በሙሐመድ ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: