ኢትዮጵያ አሁን ላይ የጀመረችው አዲስ የብልጽግና እና የስልጣኔ ጉዞ ባዶ ፉከራ ሳይሆን በመሬት ላይ በተጨባጭ የሚገለጥ የትውልድ ቃል ኪዳን መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋገጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባላንጣዎች በተናጠል ተከፋፍለው ሊያጠቁ ሲከብዳቸው ለክፋትና ለሴራ ማበራቸውን በማስታወስ፤ አዲሱን የኢትዮጵያ ስልጣኔ የመገንባቱ ሂደት በመላው ሕዝብ ዘንድ ጽኑ እምነት የተጣለበት ታላቅ ሀገራዊ እውነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም በጽኑ መንፈስ ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “ጥያቄው ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው አይደለም፤ እንደሚቻል እርግጠኞች ነን!” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
አክለውም ትልቁ ፈተናና ዋነኛው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ራዕዩን በምን መልኩና እንዴት አድርገን በተግባር እናሳካዋለን ለሚለው ስልታዊ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ መስጠት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
በመደመር እሳቤ ተጉዞ የታለመውን ሀገራዊ የከፍታ ማማ ለመጨበጥ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ እንደሌለ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለተቀመጠው ግብ መሳካት የሚያግዙ ቁልፍ መሣሪያዎችን በዝርዝር አመልክተዋል።
በዚህም መሠረት እምቅ ሀገራዊ አቅሞችን በጥልቀት መረዳት፣ የአካሄድ ስልቶችን ከግብርና ከንባብ ጋር ማጣጣም፣ ከዓለም አቀፍ የተሻሉ ተሞክሮዎችን ወስዶ ከራስ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስማማት፣ በብሔራዊ አንድነት ላይ ጸንቶ መቆም፣ የቡድን እና የግል መብቶችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስጠበቅ እንዲሁም ጠንካራ ሲቪክ ማንነትን ገንብቶ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምህዳርን በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ ማጽናት ወሳኝ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በመንግሥትና በሕዝብ የማይበገር አብሮነትና በጽናት የያዘችውን የብልጽግና ርዕይ ከዳር በማድረስ፣ የነገዋን የበለጸገችና ሉዓላዊ ክብሯ የተጠበቀ ታላቅ ሀገር ለትውልድ ማውረሷ የማይቀር ታሪካዊ እውነታ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድጋሚ አስታውቀዋል።
#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: