Search

“ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ገቢ 1 ትሪሊዮን 980 ቢሊዮን ብር ደርሷል”፦ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

ማክሰኞ መስከረም 26, 2019 73

ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በጽናት በመሻገር በታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ልዕልና እና ተጨባጭ የማድረግ አቅም እያረጋገጠች መሆኗን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ በ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር፣ ሀገሪቱ ያስመዘገበችው ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ገቢ 1 ትሪሊዮን 980 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይፋ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በመንግሥትና በሕዝብ የጋራ ትብብር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችና መርሐ ግብሮች ፍጹም ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉን እንዲሁም ባጠረ ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ያስመዘገቡት የከተሞች የተቀናጀ የዝመናና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አብነት የሚጠቀሱ ስኬቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት ያወጣቸውን ዕቅዶች በቁርጠኝነት ለመፈጸም መትጋቱ እና ማኅበረሰቡም ያለ ስስት ሐሳቡን፣ ዕውቀቱንና ጉልበቱን ማበርከቱ ለዚህ የላቀ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን የዕድገት እርምጃ እና ግስጋሴ በሚቆጠሩና በሚለኩ ጠንካራ አመላካቾች ማሳየት እንደሚገባ ያነሱት ፕሬዚዳንት ታዬ፣ የ2018 ዓመታዊ የሰብል ምርት ከሰባት ዓመታት በፊት ከነበረበት 335 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ማደጉን አመልክተዋል።

ይህ ስኬት ተራ እመርታ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታላቅ የማድረግ ልዕልና የሚያረጋግጥና ሊሞገስ የሚገባው ሁነኛ ድል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የወጪ ንግድ ገቢ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 11.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ማስመዝገቡን፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት በ15.8 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ የብድር አቅርቦት ወደ 1.3 ትሪሊዮን ብር ማደጉን እንዲሁም የዋጋ ግሽበት በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም ወደ 13.4 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን በዋነኛ ማሳያነት ዘርዝረዋል።

ይህ ታሪካዊ ውጤት የበርካታ ዜጎች ዕውቀት፣ ላብና ጉልበት የፈሰሰበት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ ድሉ የተመዘገበው በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በጽናት በመቋቋም መሆኑን አስገንዝበዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ ያቀደችው ዕድገት ጊዜያዊ ፈተናዎችን በብቃት የሚሻገር ብቻ ሳይሆን፣ የሀገሪቱን ዘላቂ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችል ተጨማሪ አቅምና ብቃት መፍጠሩን አረጋግጠዋል።

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ ሰንቃ ወደፊት የምትገሰግሰው ኢትዮጵያ፣ በልጆቿ ጥረትና በጽኑ ተቋማዊ አቅሟ ማንኛውንም የኢኮኖሚ ሴራና ጫና በመበጣጠስ የከፍታ ማማዋን ማረጋገጧን እንደምትቀጥል በፕሬዚዳንቱ ንግግር በድምቀት ተመላክቷል።

 

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: