Search

ከዓባይ እስከ ቀይ ባሕር፦ የካይሮ የማግለያ ሴራ እና የኢትዮጵያ ቁርጠኝነት

ማክሰኞ መስከረም 26, 2019 78
በዓባይ ወንዝ ላይ ፍጹማዊ የብቸኝነት መብት ይገባኛል የምትለው ግብፅ በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ተቸንክራ፣ ለዓባይ ውኃ ስትል ኢትዮጵያን ማዳከም የሚለውን ግቧን ከቀጥታ ጦርነት እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አማፅያንን ማደራጀት እና መደገፍ ቀጥላለች።
በእነዚህ ሁሉ የዓመታት የሴራ እና የማዳከም እንቅስቃሴዋ ኢትዮጵያን ከልማት እና ዕድገቷ መግታት ያልቻለችው ግብፅ፣ ዛሬም አማራጭ ያለችውን ሁሉ ከመጠቀም ግን አልቦዘነችም።
ሲደላት እና ጉዳይ ሲኖራት አፍሪካዊት፣ ሲከፋት እና ሴራ ስትሻ ዓረባዊት መሆንን የተካነችበት ግብፅ፣ በዓባይ ወንዝ ላይ የበቀለው ሕዳሴ ግድብ ተመርቆ እስኪረታት ድረስም ሆነ ዛሬ የዓባይ ወንዝን የዓረብ ብቸኛ ጉዳይ እያደረገችው ስትከስ ኖራለች። ዳሩ ግን ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ሀብታቸው ለመልማት የማንንም ፈቃድ አይሹምና ሲጫኗቸው የበለጠ እንደሚስማር እየጠበቁ ሕዳሴን ዕውን አደረጉት።
ይሁንና ግብፅ ዛሬም እውነቱን መቀበል አትሻምና በዓባይ ላይ የተሸነፈችበትን እውነት ተቀብሎ ለቀጣናዊ ትብብር ከመሥራት ይልቅ፣ ቀጣናዊ ትብብር በሚል የዳቦ ስም ኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባሕር እንዳትወጣ ያግዘኛል ያለችውን ሁሉ እያደረገች ነው። ከሰሞኑ ያደረገችውም የዚሁ ቅጥያ ነው።
የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ ጥሪ በግብፅ ኒው ኤል-ዓላሜይን ከተማ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት መካከል የሱዳን፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ መሪዎችን ሰብስባ በቀጣናዊ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ መከርን፣ የጋራ መግባባት ላይ ደረስን ብላ ያስወጣችው መግለጫ የካይሮን ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሆኗል።
በቅድሚያ ነገር በቀጣናው ሰላም እና ትብብር አዋኪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን የምታራምደው ግብፅ፣ ቀጣናዊ ትብብር እና በጋራ ማደግን እንዲሁም ለመልካም ጉርብትና ቅድሚያ የሚሰጠውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሸንፋለሁ በሚል ከንቱ ቅዠት ስለምትደክም እንጂ፣ ቀጣናዊ ትብብር የሚለው የካይሮ ስልት ከአንገት በላይ ባይሆን ኖሮ ትክክለኛ አጋሯ ኢትዮጵያ በሆነች ነበር።
ዳሩ ግን ሻዕቢያን በፍላጎቷ መልክ ቀርፃ እና የገንጣይነት ተልዕኮ ሰጥታ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር በጊዜያዊነት የነጠለችው ግብፅ፣ ከሦስቱ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት መሪዎች ጋር ተሰበሰብኩ፣ የጋራ አቋማችንም ይኸው ነው ብላ የቀይ ባሕር ጉዳይ የቀይ ባሕር ተዋናዮች ብቸኛ መብት ነው የሚል መግለጫ ስታወጣ ስትታይ፣ የስብሰባውም ሆነ አጠቃላይ የካይሮ ዓላማ ምን እንደሆነ የሚናገረው ብዙ ነው።
ቀይ ባሕር ላይ ብሔራዊ ጥቅም እና ጉዳይ አለን ብለው ያመኑ በደርዘን የሚቆጠሩ ሀገራት ከድንበራቸው ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀትን አቋርጠው ቀይ ባሕር ላይ የጦር መንደር ሲገነቡ እና ጦር ሲያሰፍሩ ተንፍሳ የማታውቀው፣ ደግሞም ዓባይ ላይ እውነትን እና የፍትሐዊነት መርሕን በያዘችው ኢትዮጵያ የተሸነፈችው ግብፅ፣ የኢትዮጵያ ቀጣይ መዳረሻ ቀይ ባሕር ነው ብላ ስላመነች ብቻ በሁለትዮሽ፣ በሦስትዮሽ እና በአራትዮሽ በሚሉ ስያሜዎች ከኢትዮጵያ በተቃራኒ መቆሜን ይደግፉልኛል ያለቻቸውን መንግሥታት ነጋ ጠባ እየጠራች በቀጣናው ደኅንነት ላይ መክረን አቋም ያዝን ስትል ራሷን እየሸወደች ትገኛለች። አዎ! የኢትዮጵያ ቀጣዩ መንገድ ግብፅ እንዳለችውም ወደ ቀይ ባሕር ነውና ይህን በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረግ ጉዞ የሚያስቆም ኃይል የለም።
መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በተመሠረተው የመደመር መንግሥት መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ይህንኑ ሐሳብ አፅንኦት በመስጠት፣ ኢትዮጵያ የጠላትን ሴራ በጣጥሳ መሻቷን በተግባር እንደምትከውን አስምረውበታል። በመሆኑም አስተማማኝ የባሕር መግቢያ እና መውጫ እንዲኖራት መንግሥታቸው በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አብስረዋል።
ለሁለቱ የኢፌዴሪ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም ንግግር ያደረጉት እና የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ያብራሩት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ በማጠናከር፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ማድረግ የቻለችውን የባሕር በር ጥያቄ በጋራ ጥቅም፣ በሰጥቶ በመቀበል እና በሰላማዊ መንገድ ዕውን እንዲሆን ጥረት ይደረጋል ሲሉ ወደ ኋላ ላይመለስ የተነሣ ጥያቄ መሆኑን ለወዳጅ እና ጠላት ቁርጡን አሳውቀዋል።
በመሆኑም በግብፅም ይመራ በሌላ አካል፣ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄን የሚያደናቅፍ አካል እየተሸነፈ እንደሚሄድ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ እንደልማዷ እያሸነፈች የቀጣናው መሪ ሀገር የመሆን ጉዞዋን ከማሳካት የሚያግዳት ኃይል እንደማይኖር እርግጥ ሆኗል።
በስንታየሁ አባተ
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: