Search

መደመር፦ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እና የዕድገት መንገድ

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 170

አንድ ሀገር የወደፊት ጉዞዋን ለመወሰን ያለፈውን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን ከታሪኳ ምን እንደምትወርስ እና ይህን ውርስ ወደ ዛሬ ልማት እንዴት እንደምትለውጥ ማወቅ አለባት።

የኢትዮጵያ ታሪክም ይህን ፈተና በተደጋጋሚ አስተናግዷል። ከማኅበራዊ እውነታዋ እና ከታሪካዊ ተሞክሮዋ የተነጠሉ ሐሳቦችን በድፍን ለመተግበር የተደረጉ ሙከራዎች አንዳንዴ ከልማት ይልቅ ለመከፋፈል እና ለግጭት መንገድ ከፍተዋል።

ከዚህ ልምድ የሚወጣው ዋና ጥያቄ አንድ ነው፤ ኢትዮጵያ የራሷን የሥልጣኔ እና የልማት መንገድ በራሷ አስተሳሰብ መቅረጽ ትችላለችን? የሚል። የመደመር እሳቤ የሚመልሰው ይህንኑ ጥያቄ ነው።

መደመር፣ በዚህ አንፃር፣ የፖለቲካ መፈክር ብቻ ሳይሆን ሀገርን በምን መርሕ እንገንባ? የሚለውን ጥያቄ የሚያነሣ ፍልስፍና ነው። እሳቤው ብዝኃነትን እንደ መከፋፈያ ሳይሆን እንደ አቅም ይመለከታል፤ አንድነትንም ልዩነትን በማጥፋት ሳይሆን ልዩነቶችን በጋራ ጥቅም በማስተባበር ይገነባል።

ይህ እሳቤ ትናንትን እንደ ተረፈ ነገር አይመለከትም። የአብሮነት ልምዶች፣ የምክክር ባህሎች፣ የመተሳሰብ እሴቶች እና ከብዙ ትውልዶች የተወረሱ የሥልጣኔ ሀብቶች ዛሬን ለመገንባት ሊውሉ የሚችሉ ካፒታሎች ናቸው።

ስለዚህ የቀድሞውን በሙሉ መቀበልም ሆነ በሙሉ መጣል ሳይሆን፣ ከተሻለው ውርስ በመነሣት አዲስ ዘመን መገንባት የእሳቤው አንዱ መሠረት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በተካሄደው የመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “መደመር የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆን እንደሚችል አረጋግጠናል” ሲሉ ይህን እሳቤ ከዕለታዊ ፖለቲካ ባሻገር ለረዥም ዘመን የሀገር ግንባታ ሐሳብ ለማሸጋገር ያለውን ምኞት ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታዩ አንዳንድ ዕድገቶች ለውጥ መኖሩን ያመላክታሉ። በ2018 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 9.2 በመቶ ማደጉ እና በ2019 ደግሞ ከ10 በመቶ በላይ እንደሚያድግ መተንበዩ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን መግለጹ ለዚህ ማሳያ ናቸው።

በዚህ ለውጥ ውስጥ አንዱ ዋና ምልክት ኢኮኖሚውን ከባህላዊ መሠረት ወደ ተለያዩ የዕድገት ምንጮች ማስፋት ነው። ግብርና፣ ማኑፋክሪንግ፣ ማዕድን፣ ኢነርጂ፣ ቱሪዝም እና ዲጂታል ኢኮኖሚ በአንድ የልማት ሰንሰለት ውስጥ እየተገናኙ መሆናቸው አዲስ የኢኮኖሚ አቅጣጫን ያሳያል።

ሌላው የሚታየው ለውጥ ዲጂታል ሽግግር ነው፤ የዲጂታል መታወቂያ፣ የዲጂታል ክፍያ እና የኢንተርኔት ተደራሽነት እየሰፉ መምጣታቸው ኢትዮጵያ ከባህላዊ ኢኮኖሚ ወደ ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት የተመሠረተ ምርታማነት ለመሸጋገር ያላትን ፍላጎት ያሳያል።

እነዚህ ሁሉ የሚያስተሣሥራቸው አንድ ሐሳብ አለ፤ ዕድገት የአንድ ዘርፍ ውጤት አይደለም። ግብርና ኢንዱስትሪን መደገፍ፣ ኢንዱስትሪ ሥራን መፍጠር፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ትምህርት የሰው ካፒታልን ማፍራት እና ተቋማት ይህን ሁሉ ማስተባበር አለባቸው። ይህ የተበታተኑ አቅሞችን ወደ አንድ የዕድገት ኃይል የማዋሃድ ሂደት ነው።

የሀገር ግንባታ ግን ችግር የሌለበት ጉዞ አይደለም። የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ዕድል ፍላጎት፣ የደኅንነት ችግሮች እና የማሻሻያ ሂደቶች የሚያመጧቸው ጫናዎች አሁንም አሉ። ስለዚህ የመደመር ፈተና ችግሮችን መካድ ሳይሆን በጋራ አቅም መፍታት ነው።

በዚህ አውድ የብሔራዊ ውይይት ሂደት ልዩ ትርጉም አለው። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከምክክሩ የተጠናከሩ አጀንዳዎችን እና ምክረ ሐሳቦችን ለባለድርሻ አካላት ማስረከቡ ውይይትን ከሂደት ወደ ተግባራዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ለማሸጋገር የተደረገ ጥረትን አመላካች ነው።

ስለዚህ መደመር በተግባር ሲታይ ሦስት ነገሮችን በአንድ ላይ ለማምጣት ይሞክራል፤ ከታሪክ መማር፣ ከልዩነት ጋር መኖር እና ወደ ዕድገት በጋራ መጓዝ። በአንድ በኩል የሀገር ማንነትን ከትናንት ጋር ያገናኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬን ከቴክኖሎጂ፣ ከኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ከዘመናዊ ተቋማት ጋር ያጣምራል።

የሥልጣኔ ጉዞ በአንድ መንግሥት ወይም በአንድ ትውልድ አይጠናቀቅም። ዛሬ የሚገነባው ተቋም፣ የሚፈጠረው ዕውቀት፣ የሚስፋፋው ምርት እና የሚጠናከረው ሰላም ነገ ለሚመጣው ትውልድ የሚተላለፍ ውርስ ነው።

በዚህ አንፃር መደመር ትልቁ የሚያቀርበው ትርጉም ይህ ነው፤ የተለያዩ አቅሞችን አንድ ላይ አድርጎ ሀገርን ወደ ፊት ማራመድ።

ስለዚህ መደመር በትክክል ከተተረጎመ የአንድ ዘመን መፈክር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ታሪኳን ሳትክድ፣ ብዝኃነቷን ሳታፈርስ እና ዘመናዊነትን ሳትፈራ የራሷን የሥልጣኔ እና የልማት መንገድ ለመቅረጽ የምትጠቀምበት ሀገር በቀል ሐሳብ ነው።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: