ኢትዮጵያ በታሪኳ በአንድ ወቅት ሁለት የባሕር በሮች የነበሯት አገር ብትሆንም፣ በተቀነባበረ የፖለቲካ ሴራ የባህር በር አልባ መሆኗ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ይህንን የታሪክ ጠባሳ ለመሻር እና ኢትዮጵያን እንደገና የባሕር በር ባለቤት ለማድረግ መንግሥት የጀመረው ጥረት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘና በአገር ውስጥም ከፍተኛ ድጋፍ እየተቸረው ይገኛል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ አሁን የምታነሳው የባህር በር ጥያቄ አዲስ ጉዳይ ሳይሆን፣ በሴራ የተነጠቀችውን መብት ለማስመለስ የምታደርገው ሕጋዊ እና ታሪካዊ ጥረት ነው።
ነዋሪዎቹ አክለውም፣ “የባሕር በር ባለቤት መሆን ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፤ ይህንን ጥረት በሰጥቶ መቀበል መርህ እውን ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
ለዓመታት የባሕር በር ማጣት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የጫነው የዋጋ ግሽበት እና ተግዳሮት ቀላል አለመሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ይህንን ችግር ለመፍታት መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በጽኑ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
የባሕር በር አለመኖር የንግድ እንቅስቃሴን በማቀዛቀዝና በውጭ ምንዛሬ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር፣ በአገር ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
“መንግሥት የባሕር በር ለማግኘት የሚከተለው ሰላማዊ እና የሰጥቶ መቀበል መርህ እጅግ አበረታች ነው” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
ይህ አገራዊ ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በመቆም ለመንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።
የባሕር በር ጉዳይ የአንድ አካል ወይም የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የገለጹት የወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች፤ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እያገኘ ያለውን ተቀባይነት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የጂኦ-ፖለቲካ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ ለቀጠናው ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የባሕር በር ጥያቄው እስከሚሳካ ድረስ በአገር ውስጥ ያለው ሕዝባዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተመስገን ተስፋዬ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: