Search

በአዲስ መንፈስ እና በጸና ማኅበራዊ ውል የተመሰረተው የመደመር መንግሥት

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 139

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው የመመሥረቻ ጉባኤ፣ የኢትዮጵያን የልማት እና የሰላም ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረው አዲሱ የመደመር መንግሥት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።

ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባች ያለውን የብልጽግና ስኬቶች ይበልጥ ለማጠናከር እና ሁለንተናዊ ከፍታዋን ለማረጋገጥ የተቀየሰ ትልቁ ሀገራዊ የሽግግር ምዕራፍ ነው።

ላለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ፈተናዎችን በጽናት እና በጥበብ በማለፍ፣ የዕድገት እና የሰላም ማዕቀፎችን ለማረጋገጥ የተደረገው ርብርብ አሁን በሚመሠረተው የመደመር መንግሥት አማካኝነት በተቀናጀ አቅም ይቀጥላል።

የመደመር ርዕዮተ ዓለም ብዝኃነትን የጥንካሬ እና የውበት ምንጭ በማድረግ በጋራ ጥረት የኢትዮጵያን ልዕልና እውን ማድረግ እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጠ መመሪያ ነው።

አዲሱ የመደመር መንግሥት ይህንን ዕሳቤ በመሠረትነት በመያዝ በሦስት ዋና ዋና የማዕዘን ድንጋዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ይንቀሳቀሳል።

የመጀመሪያው ምሰሶ ምናባዊ ራዕዮችን ወደ ተጨባጭ የልማት ፍሬ የመለወጥ የፈጻሚነት አቅም ነው።

እንደ አዲስ አበባ የኮሪደር ልማት፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና የዲጂታል ሽግግር ያሉ ተግባራት የዚሁ ፈጣን እና ውጤታማ አሠራር ማሳያዎች ናቸው።

ሁለተኛው ምሰሶ ተለዋዋጭ እና ዘመናዊ አሠራርን በመከተል የኢኮኖሚ መዋቅሩን ማዘመን፣ አምራችነትን ማሳደግ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በጽናት መምራት ነው።

ሦስተኛው እና መሠረታዊው ማዕዘን ደግሞ በሦስት ታሪካዊ ኃላፊነቶች ላይ የተገነባው አዲሱ ማኅበራዊ ውል ነው።

ይኸውም የነበረውን አዎንታዊ እሴት እና አብሮነት ጠብቆ ማቆየት፣ በታሪክ አጋጣሚ የተበላሹ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ቁስሎችን ሀገራዊ ምክክርን ጨምሮ በእውነተኛ መግባባት ማረም፣ እንዲሁም የጎደሉ ተቋማዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅሞችን ማሟላት ነው።

በመሆኑም አዲሱ የመደመር መንግሥት የተረከበው ታሪካዊ አደራ የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ልማት የረቀቀች በምሥራቅ አፍሪካ የሰላም፣ የዲፕሎማሲ እና የዕድገት ምሰሶ የሆነች ሀገር አድርጎ ለማስቀጠል ትልቅ ዋስትና የሚሰጥ ነው።

ይህ አዲስ መንግሥታዊ አወቃቀር የጋራ ተጠቃሚነትን፣ ፍትህን እና እኩልነትን በማስፈን የሁሉም ኢትዮያውያን ተስፋ እንዲሰምር ታስቦ የተዋቀረ ነው።

የጀመርነው የብልጽግና ጉዞ የሚሳካው በሁሉም ዜጎች ንቁ ተሳትፎ፣ ሰላምን ባጸና መልኩ በጋራ በመሥራት እና በሀገር ፍቅር ቆራጥነት በመሆኑ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት አሸንፋ ትቀጥላለች።

በሔዋን ጌታቸው

‎#የመደመርመንግሥት

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: