ኢትዮጵያ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን የልማት አጀንዳዋ ማዕከል በማድረግ እየሠራች ባለው ሥራ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 100 ሺሕ ሕፃናትን ከመቀንጨር መታደግ መቻሏን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በሥርዓተ ምግብ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን የኢትዮ-ናይጄሪያ የሥራ አመራር የልምድ ልውውጥ መድረክ ዛሬ አስጀምረዋል።
የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን በልማት አጀንዳ ማዕከልነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ የዚሁ ጥረት ዋነኛ አካል መሆኑንም አብራርተዋል።
በሰቆጣ ቃል ኪዳን የመፍትሔ ማፈላለጊያ ምዕራፍ በተመረጡ አካባቢዎች የሕፃናትን መቀንጨር በዓመት በአማካይ እስከ 3 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በማስፋፊያ ምዕራፉ ደግሞ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 100 ሺሕ የሚጠጉ ሕፃናትን ከመቀንጨር መታደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ይህ አበረታች ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ በተጠናከረ ኢንቨስትመንት፣ በማኅበረሰብ ተሳትፎና በተቋማዊ አሠራር ላይ በተሰጠ ልዩ ትኩረት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያና ናይጄሪያ የሥርዓተ ምግብ አመራር የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ የተሳተፉት የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የሕፃናት መቀንጨርን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ሥራ አድንቀዋል።
በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግርም፣ ኢትዮጵያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካኝነት በ2030 ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ከመቀንጨር ለመታደግ ያላት ራእይ አስደናቂ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ "በአንድ ግብ፣ አንድ ዕቅድ እና አንድ በጀት" መርህ በመንግሥት ባለቤትነትና በአጋሮች ተሳትፎ የምታካሂደው ሥራ በሕፃናት ላይ ብሩህ ተስፋ የሚያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ እየተተገበረ ያለው ይኸው የሰቆጣ ቃል ኪዳን በ15 ዓመታት ውስጥ ማለትም በ2030 ከሁለት ዓመት ዕድሜ በታች ባሉ ሕፃናት ላይ የሚከሰትን መቀንጨር ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአሸናፊ እንዳለ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: