Search

የነገን ሥልጣኔ በዛሬው ትጋት፦ የመደመር መንግሥት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 172

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ያደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያን ከተግዳሮት ወደ የላቀ ሥልጣኔ የማሸጋገር ራዕይን በግልጽ የሚያንጸባርቅ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው 54 ሚሊዮን ዜጎች በምርጫው ወቅት የነበረውን ውዥንብር እና ወከባ ተቋቁመው ለዴሞክራሲ ግንባታ ያሳዩትን ጽናት በማድነቅ ሐሳባቸውን ይጀምራሉ።

ከምርጫው ማግስት 'አሸናፊ እና ተሸናፊ' በሚል ስሜት ሳይከፋፈሉ ሁሉም ዜጋ እንደ ወንድማማች ተያይዞ እኩል ሊራመድ እንደሚገባ አሳስበው፣ ሀገራዊ አንድነትን በማጽናት ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ማሻገር የመንግሥታቸው ዋነኛ ማጠንጠኛ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት የዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ መልክ እጅግ ፈጣን በሆነ የሽግግር እና የአይገመቴነት ማዕበል ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ዓለም ባለብዙ ዋልታ ለመሆን በሚያደርገው የጂኦፖለቲካ ትግል መሐል ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ያለችውን ዓለም ሁኔታ በሚገባ ተገንዝባ ቀድማ መዘጋጀት እንዳለባት ነው ያስጠነቀቁት።

ባለፉት የኢንዱስትሪ አብዮቶች ወቅት በውስጥ ግጭት እና መዘናጋት ያጣናቸውን ዕድሎች ያለመዘጋጀት ያስከፈለንን ዋጋ የዛሬው ትውልድ ሊማርበት ይገባል።

በተለይም በቀይ ባሕር፣ በሕንድ ውቅያኖስ እና በአፍሪካ ቀንድ መገናኛ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ካላት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ አኳያ ወጥቶ መግቢያ የባሕር በር እንዲኖራት መሥራት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተውበታል።

ይህን ሰፊ ራዕይ ለማሳካት፣ የውጭ ሐሳቦችን በቀጥታ ከመቅዳት ይልቅ ከኢትዮጵያዊ አውድ ጋር የተጣጣመውን የ"መደመር" እሳቤን መተግበር አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን በንግግራቸው አስምረውበታል።

ይህ እሳቤ ብዝኃነትን ከአንድነት በማጣመር ጠቅላይ እና ከፋፋይ ትርክቶችን በኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ይተካል።

አዲስ ሲቪክ ማንነትን በመገንባት እና ዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩን ለማስፋት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በብሔራዊ ጥቅም ላይ አብሮ ለመሥራት መንግሥታቸው ጠንካራ ፍላጎት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያሰባሰባቸውን ምክረ ሐሳቦች መነሻ በማድረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚው መስክ ከአንድ ዘርፍ ጥገኝነት ወደ ተቀናጀ የብዙኃ ዘርፍ አካሄድ መሸጋገር የሪፎርሙ ማዕከል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል።

ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ እና ማዕድንን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዘርፎች የተጀመሩ ማሻሻያዎች ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የበጋ መስኖ ልማትን በማስፋፋት በስንዴ፣ በሩዝ እና በሌሎችም ምርቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ርብርብ የለውጡ ማሳያ መሆኑን አውስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የውኃ መብታችንን የማስከበር ጽናታችንን ያረጋገጠ ታሪካዊ ድል መሆኑን፣ እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያን መገንባት፣ የኮሪደር ልማት እና 56 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎቻቸው መሆናቸው ተዘርዝሯል።

ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሰላም፣ ደኅንነት እና ጠንካራ ተቋማዊ አሠራር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አበክረው ገልጸዋል።

በጫካ ያሉ እና ያኮረፉ ወገኖች በይቅርታ መንፈስ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ የጠየቁ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣናው የአየር የበላይነት ሊፈጥር የሚችል ዘመናዊ እና ብቁ የመከላከያ ኃይል ግንባታ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

የዜጎችን ሕይወት የሚፈታተነውን የኑሮ ውድነት ከመቅረፍ ባለፈ፣ ሌብነትን እና ሙስናን በጽኑ ለመዋጋት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን እስከ ታችኛው እርከን ማውረድ የግድ እንደሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የሚዲያ ምኅዳሩ፣ የሃይማኖት እና የሲቪክ ማኅበራትም ሕግን እና ብሔራዊ እሴትን በማክበር ለሥልጣኔ ግንባታው የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ጠንካራ የቀጣናው ምሰሶ ሆና እንድትወጣ ግልጽ ራዕይ ያስቀመጠ ነው።

ይህ የትውልድ ቃል ኪዳን ዕውን የሚሆነው ወጣቶች ነገን በአርቆ አሳቢነት ሲቀርጹ፣ እናት እና አባቶች ታሪክን ሲያስተላልፉ፣ እንዲሁም ፓርላማው የሕዝብን ሕይወት ለውጥ በቅርበት ሲከታተል እንደሆነ ዶክተር ዐቢይ አስገንዝበዋል።

ድህነትን ማሸነፍ፣ ትምህርት እና ጤናን ማዳረስ የመንገዱ ማሳለጫዎች እንጂ የመጨረሻው ግብ እንዳልሆኑ፤ የመጨረሻው ግብ "አዲስ እና ዘላቂ ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔን መገንባት" መሆኑን አስምረውበታል።

ለዚህ ደግሞ ትናንትን ለማስተካከል እና የነገን ሥልጣኔ ለመቅረጽ ቁልፉ መፍትሔ "ዛሬን በትክክል መሥራት" መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው በሚገባ አብራርተዋል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: