የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
የመንግሥት ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ ግልጽ እና ውጤታማ የሆነ የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት በመፍጠር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና የተጠሪ ተቋማት የጋራ እና የተናጠል ተግባር በግልጽ በማስቀመጥ ረገድ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
የመንግሥት ተወካይ እና አስረጂ የሆኑት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ሃና አርዓያሥላሴ የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት እና ዓላማን በተመለከተ በዝርዝር ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት መሥሪያ ቤቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የታዩትን ውስንነቶች ለመቅረፍ ረቂቅ አዋጁ እንደሚያግዝ እና የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እና የአገልግሎት ዘርፉን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ረቂቅ አዋጁ ሰፊ ጥናት የተደረገበት እና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ በቂ ግብዓት ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል።
የተቋማትን አደረጃጀት በግልጽ ማስቀመጥ፣ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብትን የሥራ ኃላፊዎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ረቂቅ አዋጁ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ አንዳንድ የተጠሪ ተቋማት ለውጥ በደንብ የሥራ ባሕሪያቸውን እና ያላቸውን ፋይዳ ያገናዘበ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ቀልጣፋ እና ውጤታማ አደረጃጀት በመፍጠር የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት አያይዘውም መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ምክር ቤቱ ባካሄደው ልዩ ስብሰባው፣ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1440/2019 ዓ.ም አድርጎ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: