Search

ከፖለቲካ ልዩነት በላይ ለሆነው ብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆም

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 163

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመልሱ ቁልፍ ተግባራት ላይ የመሥራት ታሪካዊ ኃላፊነት ተረክቧል።

ይህ የሥራ ዘመን ከቀደሙት ምክር ቤቶች በተለየ መልኩ ዘመናዊ የአሠራር ለውጦችን፣ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎችን እና ጥልቅ ብሔራዊ ሪፎርሞችን የሚያስተናግድ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በተለይም ከሀገራዊ ምክክር የተገኙ የማሻሻያ ምክረ ሀሳቦች በምክር ቤቱ የሚደመጡ ሀሳቦች እና ድምፆች ስብጥር ይበልጥ ሰፊና ህያው እንደሚሆን ይታመናል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተግባር የሕግ አውጭነት ሚናውን ከመወጣት ባለፈ፣ አስፈጻሚው አካል የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለሱን እና የመንግሥት የልማት ዕቅዶች መከናወናቸውን መከታተል፣ መቆጣጠር እና መገምገም ነው።

በዚህ ሂደት የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ አዳዲስ የልማት ሥራዎችን ማስጀመር እና የሥራ አፈጻጸም መረጃን በግልጽነት ለሕዝብ ማድረስ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ይህን የቁጥጥር ሥርዓት ለማጠናከር ከመንግሥት እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት መሥራት የተሻለ እና ጠንካራ የምክር ቤት ባህል መገንባት ወሳኝ ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከባሕር በር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ እና የሕዝብ ቁጥሯ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ያለ የምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ አካል መሆኗን ተከትሎ የባሕር በርና የውኃ ሀብት አጠቃቀም ጉዳዮች የህልውናና የልማት መሠረት ናቸው።

ስለሆነም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥቅም ለማስከበር በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በሰላማዊ መንገድ አብሮ የመኖር ባህል፣ በዲፕሎማሲያዊ ንግግር እና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ በተመሠረተ የሰጥቶ መቀበል አማራጭ መሥራት እንደሚገባ ተወካዮቹ ያሰምሩበታል።

በተለይም በፖለቲካ ሐሳብና በፖሊሲ አማራጮች መካከል ያለው ፉክክር እንደተጠበቀ ሆኖ በብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚደረግ የጋራ ትብብር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ያጠናክራል።

“የፖለቲካ ፓርቲያችን ቢለያይም ያለችን ኢትዮጵያ አንድ ነች፤ የምንሠራውም ለአንድ ሕዝብ ጥቅም ነው” የሚሉት የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ልዩነታቸውን ጠብቀው በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ በጋራ እንደሚሠሩ ያረጋግጣሉ።

ይህ አቋም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የትብብር እና የፉክክር መስመርን ለይቶ የመጓዝ አዲስ ባህል የሚያጎለብት እና ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ነው።

በኢንቲሃድ አብራር

#የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: