Search

የምግብ ዋስትና እና ብሔራዊ ክብር፡ የግብርናው ዘርፍ የተጓዘበት የድል መንገድ

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 127

ባለፉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ የግብርና ሥርዓት ሀገራዊ ገጽታውን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀይር፣ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ እና የታሪክ አቅጣጫውን የቀየረ ሰፊ መዋቅራዊ ለውጥ አስመዝግቧል።

በተለይም በበጋ መስኖ ልማት የተከናወኑ ግዙፍ እና መሬት ላይ የተረጋገጡ ሥራዎች የኢትዮጵያን የስንዴ እና የሩዝ ምርት ታሪክ በአዲስ መልክ የጻፉ ሲሆን፣ የሀገራችንንም የምርት አቅም ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረዋል።

ከዚህ ቀደም ከውጭ በዕርዳታ እና በግዥ ይገባ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ በስፋት አምርቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ትችላለች" ሲሉ ያስቀመጡትን ግብ በተግባር ያረጋገጠ ታሪካዊ እውነት ሆኗል።

ይህ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የ4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሽፋን ማሳካት የተቻለበት ስኬት፣ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን የመቻል አቅሟን በተጨባጭ ያሳየችበት ማረጋገጫ ነው።

በዚሁ መዋቅራዊ ሽግግር አጠቃላይ የሰብል ምርት ቀደም ሲል ከነበረበት 335 ሚሊዮን ኩንታል በአሁኑ ወቅት ወደ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ማደጉ የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ጥልቀት ያሳያል።

ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን የተበሰረው የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በኢኮኖሚው እና በማኅበረሰቡን አኗኗር እና ጤና ላይ ያሳደረው በጎ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።

የወተት፣ የዶሮ፣ የዕንቁላል እና የማር ምርትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የዜጎችን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት በእጅጉ ማሻሻል ተችሏል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የወተት ምርት ከ7.1 ቢሊዮን ሊትር ወደ 15.7 ቢሊዮን ሊትር፣ የእንቁላል ምርት ከ3.2 ቢሊዮን ወደ 11.7 ቢሊዮን፣ የማር ምርት ከ146.7 ሺህ ቶን ወደ 428 ሺህ ቶን፣ እንዲሁም የዶሮ ሥጋ ምርት ከ90 ሺህ ቶን ወደ 253 ሺህ ቶን ከፍ ብሏል።

በዘርፉ የተተገበሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች፣ የተሻሻሉ የምርት ግብአቶች አቅርቦት እና የመስኖ መሰረተ ልማቶች ማስፋፋት የሀገራችንን የግብርና ምርታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳድገውታል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳመለከቱት በ2019 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ10.1 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንን ግብ ለማሳካት እና ከተረጂነት በመላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ ጥራትን መሰረት ያደረገ መዋቅራዊ ሽግግር የማምጣት እና በምርት ግብአቶች ራስን የመቻል አቅም የማደራጀት ስራዎች በልዩ ትኩረት ይከናወናሉ።

የመደመር መንግሥት የግብርና ግብአቶችን ተደራሽነት እና ዘመናዊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማጠናከር የኢትዮጵያን አጠቃላይ የምርት አቅም ዘላቂ ለማድረግ ሰፊ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ዘመናዊ የአሠራር ስልቶችን ማስፋፋት፣ አርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን በቴክኖሎጂ ማጠናከር፣ እንዲሁም የምርት እሴት ሰንሰለትን ማሳደግ የቀጣይ ጉዞ ቁልፍ ማዕዘናት ናቸው።

የግብርናውን ዘርፍ ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ጋር በማስተሳሰር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ሥነ-ምህዳር መገንባት ተችሏል።

የመስኖ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጥንካሬ እና የገበያ ትስስር አውታሮች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ከፍታ የሚያረጋግጡ ዋና ዋና አዕማድ ናቸው።

አሁን የተገኘውን ድል አስጠብቆ በይበልጥ ማጠናከር እና ኢትዮጵያን የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች የአህጉራችን ማዕከል ማድረግ የሁሉንም ዜጋ የተቀናጀ ኃላፊነት ይጠይቃል።

በሔዋን ጌታቸው

#የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: