Search

የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ፡ ከፖሊሲ ራዕይ ወደ ግዙፍ የምርት እና የኢኮኖሚ ምሰሶነት

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 102

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሪፎርም የአምራች ኢንዱስትሪውን መዋቅራዊ አቅም በማጠናከር ለምርት ዕድገት፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት እና ለሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ አስተማማኝ መሠረት እየጣለ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፉን ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ወደ ተጨባጭ እሴት የሚጨመርበት የምርት ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የተያዘውን ሀገራዊ አቅጣጫ በላቀ ደረጃ እያጠናከረው መጥቷል።

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በውጭ ንግድ እና በኢንቨስትመንት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማዕቀፍ አንጻር አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉ ጥሬ ዕቃን በሀገር ውስጥ በማቀነባበር እሴት እንዲጨምር፣ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ትስስር እንዲጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ አቅም እንዲጎለብት የሚያስችል የኢኮኖሚ ለውጥ ዋና ሞተር ሆኖ እያገለገለ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በዘርፉ የተመዘገቡት አበረታች የቁጥር መረጃዎች የዚሁን መዋቅራዊ ሽግግር ስኬት በተጨባጭ ያረጋግጣሉ።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው አማካይ ዕድገት ከ5.5 በመቶ ወደ 12.7 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፣ የአምራች ተቋማት የማምረት አቅም አጠቃቀምም ከ47 በመቶ ወደ 69.3 በመቶ አድጓል።

በተመሳሳይ የአምራች ዘርፉ የውጭ ገበያን በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

የኤክስፖርት ገቢ ከ308 ሚሊዮን ዶላር ወደ 607.2 ሚሊዮን ዶላር ያደገ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካት የዳነ የውጭ ምንዛሪ መጠን ደግሞ ከ640 ሚሊዮን ዶላር ወደ 5.96 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። የሀገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ድርሻም ከ30 በመቶ ወደ 46.41 በመቶ አድጓል።

አዲስ ወደ ሥራ የገቡ ኩባንያዎች ቁጥር ከ112 ወደ 165 ከፍ ማለቱ እና በአምራች ኢንዱስትሪው የተፈጠረው የሥራ ዕድል ከ45 ሺህ 550 ወደ 448 ሺህ 717 ማደጉ፣ ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማነቃቃት ባሻገር የዜጎችን የገቢ እና የሥራ ዕድል በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ድርሻ እየተጫወተ መሆኑን ያመላክታል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ የሚያጋጥሟትን ጊዜያዊ ፈተናዎች በብቃት በመሻገር ዘላቂ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በ2019 በጀት ዓመት ትልልቅ ግቦችን አስቀምጣለች።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በንግግራቸው እንዳመለከቱት፣ በ2019 በጀት ዓመት ከአምራች ኢንዱስትሪ የውጭ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን በመላው ሀገራችን በማስፋፋት የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት እና የግብርና-ኢንዱስትሪ ትስስርን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

የልማት ሂደቱ ከጽኑ የፖሊሲ ራዕይ ተነስቶ በሥራ እና በምርት በተግባር እየተረጋገጠ እንደሚገኝ የሚያሳየው ይህ ጉዞ፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተወዳዳሪ የምርት እና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ታላቅ ህልም እውን እየሆነ መምጣቱን ያበስራል።

በኢንቲሃድ አብራር

#የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: