Search

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ “የኢትዮጵያን ብሩህ መንገድ የሚያመለክቱ” ሲሉ የገለጿቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ረቡዕ መስከረም 27, 2019 74

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ቀጣይ የመንግሥት እን የሥራ አቅጣጫ አመላክተዋል፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎችንም ዳስሰዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎችን የተመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ የግብርና ሥርዓቱን ለማሻሻል የተተገበሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የአምራች ኢንዱስትሪ አቅም ከፍ ማለት፣ የማዕድን ዘርፍ ልማት መስፋፋት፣ የውጭ ንግድ እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማደግ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማት አውታር መስፋፋት እና የአገልግሎት ዘርፍ ማደግ የኢትዮጵያ አማካይ ኢኮኖሚ ምጣኔ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ ከፍ ያለ ሚና መጫወታቸውን አንሥተዋል።

ፕሬዚዳንት ታየ ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ልማት ሥራዎች የተመዘገቡ ስኬቶችንም ዳስሰዋል።

በዚህም በግብርናው ዘርፍ በ2011 ዓ.ም ከነበረው 335 ሚሊዮን ኩንታል ዓመታዊ የሰብል ምርት ወደ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል መድረሱን፣ የውጭ ንግድ ገቢ 11.2 ቢሊዮን ዶላር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አብራርተዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት፣ የኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ የዲጂታል መሠረተ ልማት እና የቱሪዝም መዳረሻዎች መስፋፋት ለሀገራችን የኢኮኖሚ ከፍታ ሁነኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን አንሥተዋል።

እነዚህ ስኬቶች በውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች ውስጥ ታልፎ የተመዘገቡ በመሆናቸው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና ፈተናዎችን የመቋቋም አቅም ማሳያ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በጥልቀት ሐሳብ መመራት፣ ችግሮችን አስቀድሞ መለየት፣ ፍቱን እና ተሻጋሪ መፍትሔ ማዘጋጀት የኢትዮጵያን ብሩህ መንገድ የሚያመለክቱ መሆናቸውን ነው ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ የገለጹት።

ለ2019 ዓ.ም የመደመር መንግሥት የያዛቸውን ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እና ግቦች ሲያብራሩም፣ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን፣ ኅብረትን እና ትብብርን ማስፈን፣ ጥራትን መሠረት ያደረገ መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ፣ የትምህርት፣ የጤና እና የማኅበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን በጥራት ማሳደግ፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ወደ 65 በመቶ፣ የጤና መድኅን ሽፋንን ወደ 85 በመቶ፣ የተማሪዎች ምገባ ሽፋንንም ወደ 70 በመቶ ማሳደግ እንደሚገኙበት አንሥተዋል።

በተጨማሪም አጠቃላይ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት አንፃር ወደ 9.62 በመቶ ከፍ እንዲል፣ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አኃዝ እንዲወርድ እና አጠቃላይ የታክስ ገቢም ከፍ እንዲል እንደሚሠራ አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ዕድገቱን 10.1 በመቶ ማድረስ፣ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶችን መሳብ እና ሀገራችን የምታስተናግደውን 32ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በስኬት ማካሄድ ዋና ዋና ግቦች እንደሆኑ ገልጸዋል።

እነዚህን ግቦች ለማሳካት የሚከተሏቸውን መፈጸሚያ መንገዶች ሲዘረዝሩ፦ የፖለቲካ ልምምዳችን ከብረት እና ከአመፅ ጎዳና ተላቅቆ በሰላም፣ በንግግር፣ በዕውቀት እና በሀገራዊ ምክክር ውጤቶች ላይ እንዲመሠረት ማድረግ፣ ሌብነት እና ሙስናን በጽናት መታገል፣ ከተመዘገቡ መልካም ልማዶች በመነሣት አፈጻጸምን ማላቅ እና የመከላከያ እና የጸጥታ ኃይሎችን አቅም በማጠናከር የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር እንደሆነ አስምረውበታል።

ምክር ቤቱ የሕዝብ የይሁንታ ድምፅ እና የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ መሆኑን በመጥቀስ፣ አባላቱ የተጣለባቸውን ታላቅ አደራ በመረዳት ሕዝብን በታማኝነት፣ በዕውቀት እና በታታሪነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

በተለይም መልካም አስተዳደርን የሚያዘምኑ፣ ኢኮኖሚን የሚያሳድጉ፣ የምርት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ፣ የኑሮ ውድነትን የሚገሩ እና የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚያጸኑ ሕጎች እና አሠራሮች ላይ ትኩረት እንዲደረግም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

በዓይናለም ሃድራ

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: