የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን ጨምሮ የዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ገጽታዎች በፍጥነት እየተለዋወጡ ባሉበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ መድረክ እንደገለጹት፣ የዘመናችን ፖለቲካዊ እና ጂኦፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የዓለምን መልክና ጸባይ በፍጥነት እየቀየሩት ነው።
በመሆኑም ኢ-ተገማችነት የአሁኑ ዘመን ዋነኛ መገለጫ ሆኗል ማለት ይቻላል።
እነዚህ ያልተጠበቁ ፈጣን ለውጦች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስኮች ተልቅ ተጽእኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።
እንዲህ ባለው ተለዋዋጭ ዓለም፣ ሀገራት ያሉበትን ሁኔታ በትክክል ተረድተው አስቀድመው መዘጋጀታቸው የሕልውናቸው ማረጋገጫ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለጋጠሟት ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ለውጦች እና ተግዳሮቶች በበቂ ሁኔታ ባለመዘጋጀቷ ዋጋ መክፈሏን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
አሁን ላይ ግን ካለፉት ታሪካዊ ስህተቶቿ ተገቢውን ትምህርት በመውሰድ ሊያጋጥሟት ለሚችሉ ማናቸውም ተግዳሮቶች እና ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጓን አብራርተዋል።
ይህ ቅድመ ዝግጅት በኢኮኖሚ ራስን ከመቻል አንስቶ ሀገራዊ ደህንነትን፣ ቴክኖሎጂን እና ዲፕሎማሲን ጨምሮ በርካታ ዘርፎችን ያካተተ ነው።
ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ኢ-ተገማች በሆኑበት በዚህ ወቅት፣ እንደ ሀገር የሚመጡ ፈተናዎችን በስኬት መሻገር የሚቻለው በተጠናከረ ሀገራዊ አንድነት እና በበቂ ቅድመ ዝግጅት ነው።
የውስጥ አንድነትን ማጠናከር የትኛውንም ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫና ለመመከት ወሳኝ ሲሆን፣ በዕቅድ እና በስትራቴጂ አስቀድሞ መዘጋጀት ደግሞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ያስችላል።
ይህ አካሄድ ኢትዮጵያ በአዲሱ የዕድገት እና የሥልጣኔ ጉዞዋ በሁለንተናዊ መልኩ ራሷን ችላ በመቆም ጥቅሟን እና ሕልውናዋን እንድታስከብር የሚያስችላት ነው።
በሃና ምንዳሁን
#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: