Search

በአብሮነት የጸናች ሀገር፦ የኢትዮጵያ የብልጽግና እና የድል ጉዞ

ዓርብ መስከረም 29, 2019 125

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በባህል፣ በታሪክ እና በዕሴት ተሣሥረው የጸኑባት፣ የብዝኃነት ውበት የጎላባት ታላቅ ሀገር ናት።

የዚህች ሀገር እውነተኛ ሀብት እና የማይናወጥ ኃይል የሚመነጨውም ከልዩነቶቿ ውበት ባሻገር በፈተና ሰዓት አብሮ በመቆም፣ ሉዓላዊነቷን በጋራ በማስጠበቅ እና የዘመናት አብሮነቷን በማጽናት ላይ ነው።

ታሪክ እንደሚያስተምረን ሀገራችን በተለያዩ ወቅቶች የገጠሟትን ከባድ ፈተናዎች እና ውጣ ውረዶች በድል ማለፍ የቻለችው በዚሁ የጸና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና በመተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ ጸንታ በመቆየቷ ነው።

ዛሬ ላይ በልማት፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በአረንጓዴ ልማት እና በሌሎችም ዘርፎች እያስመዘገብናቸው ያሉት ታሪካዊ ድሎች ትልቁ ምስክር የዚሁ የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ነው።

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የማከናወን አቅም የውጭ ሀገራትም ሆኑ የውጭ ኃይሎች የተጠራጠሩበት፣ “አይደረግም፣ አይሳካም” ተብሎ የተገመተውን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነን ስንነሣ ምን ያህል ማማ ላይ መድረስ እንደሚቻል በግልጽ ያሳየንበት የዘመናት አውድ ነው።

የሕዳሴው ግድብ የብዙኃኑ አብሮነት፣ የፋይናንስ አስተዋፅኦ እና የቁርጠኝነት ማሳያ በመሆን የኢትዮጵያን ጽናት ያረጋገጠ ትልቁ የድል አድራጊነት የማዕዘን ድንጋይ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ መወየቧን ለጠበቁ ፍካቷን፣ ድህነቷን ለሚሹ ዕድገቷን፣ አዝጋሚ እርምጃዋን ለቋመጡ ፈጣን ሩጫዋን እያሳየች፤ ከታሪክ መሠረዟን ሲጠብቁ ታሪክ እየሠራች፤ በእምርታ ወደፊት ቀጥላለች" ሲሉ የገለጹት፡፡

ሆኖም ሀገርን ከፍታ ማሳየት የሚቻለው የሰላም፣ የዕድገት እና የጋራ ርዕይ ሰንሰለትን በአንድነት ማጠናከር ሲቻል ብቻ ነው።

በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር "እንደ ሀገር የሚጠብቀንን ፈተና መሻገር የምንችለው እንደ ወንድማማቾች ተያይዘን መራመድ ስንችል ብቻ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ መልዕክት የኢትዮጵያን ሰላም፣ ደኅንነት እና ሁለገብ ዕድገት ለማረጋገጥ ቁልፍ መንገድ ነው። ፈተናዎች ሲያጋጥሙ በጥርጣሬ ሳይሆን በመተማመን፣ በመለያየት ሳይሆን በመደመር መንፈስ ተባብሮ መቆም የኢትዮጵያውያን ትልቁ መገለጫ ነው።

የሀገር ግንባታ ሂደት የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ እና የተቀናጀ ክንዳቸውን በማበርከት የሚሳካ እንጂ በተለያየ መንገድ የሚጓዝ አይደለም። ልዩነቶቻችንን እንደ ማሰሪያ እንጂ እንደ መለያያ ካልተጠቀምንባቸው፣ ነገ የምንረከባት ሀገር ከምንጊዜውም በላይ የሠለጠነች እና የበለጸገች ትሆናለች።

ለቀጣይ የዕድገት እና የብልጽግና ጉዟችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ይበልጥ ማጠናከር፣ የፍቅር፣ የሰላም እና የትብብር ዕሴቶችን በልዩ ሁኔታ ማስረፅ የሁሉንም ዜጋ የዕለት ተዕለት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

ተያይዘን ስንቆም እና እንደ ወንድማማቾች አብረን ስንጓዝ፣ የኢትዮጵያ ከፍታ የማይቀር እና ትውልዱ የሚረከባት የበለጸገች ሀገር ዕውን መሆኑ እርግጠኛ ነው። ኢትዮጵያ በልጆቿ አብሮነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሁሌም አሸናፊ ሆና ትቀጥላለች።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: