Search

የኑሮ ጥራትን እያሻሻለ የሚገኘው የየካ ጣፎ ኮሪደር ልማት

ዓርብ መስከረም 29, 2019 107

በኢትዮጵያ ከተሞች እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ውጫዊ ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ጥራት እና የመዝናኛ ሥፍራዎች ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል።

በተለይም ቀድሞ የቆሻሻ መከማቻ እና የጨለማ ሥፍራ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ ውብ እና ዘመናዊ ፓርኮች የመቀየር አቅም እንዳለው በተግባር እየታየ ነው።

ከጥቂት ጊዜያት በፊት በሸገር ከተማ የካ ጣፎ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የወንዝ ዳርቻ በተደራረበ ቆሻሻ የተበከለ እንዲሁም ለሕዝብ ጤና እና ጸጥታ ከፍተኛ ስጋት የነበረ ስፍራ ነበር።

አሁን ላይ ግን የተፈጥሮ መልክዓ ምድሩን ከዘመናዊ የሕንፃ ጥበብ ጋር በማቀናጀት የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ የመዝናኛ ስፍራ መፍጠር ተችሏል።

የካ ጣፎ ክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደስታ ዋሪቱ እንዳሉት ሥፍራው ከዚህ ቀደም የከተማው ቆሻሻ በሙሉ የሚጣልበት እና ሰው የሚሸሸው ቢሆንም ዛሬ ላይ ለከተማዋ ነዋሪዎች እፎይታን የሚሰጥ ዘመናዊ የወንዝ ዳር ፓርክ ሆኗል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እና መሪነት እየተከናወነ የሚገኘው ኮሪደር ልማት የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ እና ማኅበራዊ ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ቀይሮታል።

በፓርኩ ውስጥ ካፌዎች፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ የሕፃናት መጫወቻዎች እና ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተካትተዋል።

የኢትዮጵያን የጀግንነት እሴት በተለይም የዓድዋን ድል ለትውልድ የሚያስተላልፉ ምስሎች እና የሙዚየም ሥራዎች ስፍራውን ይበልጥ አድምቀውታል።

የተጀመረው የዓሳ እርባታም ፓርኩን ከመዝናኛነት ባሻገር የኢኮኖሚ እና የጥናት ማዕከል እንዲሆን አስችሎታል።

ወደ 3.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግረኛ መንገድ ለነዋሪዎች በእግር የመንቀሳቀስ እና ንጹሕ አየር የመተንፈስ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

የመሬቱን አቀማመጥ የተከተሉ ሰው ሠራሽ ፏፏቴዎች፣ ግዙፍ ምግብ ቤቶች፣ እግር ኳስ ሜዳ፣ የፑል መጫወቻዎች እና የሩጫ ትራክን ያካተተ የስፖርት ማዕከል መገንባቱም ወጣቶች ጊዜያቸውን በጤናማ መንገድ እንዲያሳልፉ አድርጓል።

በሁለተኛው ምዕራፍም 378 ዘመናዊ የመንገድ መብራቶችን የመትከል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በመሠረተ ልማት ረገድ እስከ 66 ሜትር ስፋት እና 70.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶች ደረጃቸውን ጠብቀው እየተገነቡ ይገኛሉ።

ይህም የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ እና ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ከመገንባት ባለፈ የንግድ እንቅስቃሴን በማነቃቃት ለበርካታ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏል።

በከተማዋ እየታየ ያለው ለውጥ ከስጋት ወደ ሰላም፣ ከቆሻሻ ወደ ውበት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከማንነት መሸርሸር ወደ ሀገራዊ ኩራት ያሸጋገረ ታላቅ የልማት ምዕራፍ ነው።

በላሉ ኢታላ                                       

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: