Search

“እማማን ለማን ልተዋት?”፦ የኢትዮጵያ ወታደር የማይሰበር ወኔ

ዓርብ መስከረም 29, 2019 247

"አንበሶቼ… ተራራ ላይ እየወጣሁ እገኛለሁ። የምር... የምር በጣም ደክሞኛል። ያው ምን ላድርግ እሺ? ኢትዮጵያን፣ እማማን ለማን ልተዋት? እ...? ለማን? ለማን ልተዋት እሷን? በጣም ነው እኮ የምወዳት። ለሷ ብዬ ነው፤ ለእናቴ ብዬ... ለእናት ሀገሬ ብዬ... እወድሻለሁ እማማ... ሁሌም እወድሻለሁ፤ እጠብቅሻለሁ! መቼም... መቼም ቢሆን ተስፋ አልቆርጥም እማማ!…"

መቼም ከላይ የሰፈረውን የአንድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መልዕክት ብዙዎቻችሁ ሳትሰሙ አትቀሩም። የዚህ ጀግና ወታደር እውነታ የሁሉም የኢትዮጵያ ጀግኖች ወታደሮች እውነታ ነው።

ምንም ያህል ቢደክመው፣ ከባዱን ተራራ መውጣት፣ አስቸጋሪውን ገደል መውረድ፣ የሚፋጀውን የፀሐይ ሐሩር ችሎ ማለፍ አላቃተውም፤ ምክንያቱም ብርታቱ የሆነ አንድ ታላቅ ቃል ልቡ ውስጥ አለና - ኢትዮጵያ!

“ኢትዮጵያን፣ እማማን ለማን ልተዋት?” የሚለው ጥያቄው የዘመናችን ወታደር ብቻ ሳይሆን ከዘመናት በፊት በየጦር ሜዳው የወደቁትን የአባቶቹን እና የእናቶቹን ጽናት የሚያስተጋባ መልዕክት ነው።

የኢትዮጵያ ወታደር ድካም አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ቢሰማውም፣ ለሀገሩ ያለው ፍቅር ግን ከድካሙ በላይ ገዝፎ ተራራውን ያሳንሰዋል፤ ገደሉን ሜዳ ያደርገዋል።

ይህ ስብዕና የተገነባው ታዲያ በአንድ ጀምበር አይደለም፤ በዓድዋ ተራሮች ላይ በባዶ እግሩ ጠላትን የሽንፈት ጽዋ ካቀመሰው ዐርበኛ እና በካራማራ የሀገሩን ዳር ድንበር በደሙ ካስከበረው የቁርጥ ቀን ልጅ ጋር ጥልቅ የሆነ የደም እና የመንፈስ ትሥሥር አለው።

ይህ ስብዕና የማይበጠስ የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት ነው፤ የአያት ቅድመ አያቱ ዐርበኝነት በደም ሥሩ የሚፈስስ፣ ሀገር የማዳን ወኔ በልቡ ውስጥ የሚንቀለቀል ትውልድ ያላት ሀገር ናት - ኢትዮጵያ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን እውነታ በሚመሰክር መልኩ በተደጋጋሚ ሲናገሩ፣ “የኢትዮጵያ ወታደር ያለውን ልብ ማንም ወታደር የለውም” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ወታደር ከውጭ ባዳዎችም ሆነ ከውስጥ ባንዳዎች የሚገጥሙትን ፈተናዎች ድል ማድረግ የሁልጊዜ ተግባሩ ነው። የሀገርን ሉዓላዊነት ሊደፍር፣ ክብሯን ሊያዋርድ ከፊት ለፊቱ የሚመጣውን ባዳ በጀግንነት ይመክታል፤ ይህ ግልጽ የሆነ እና ደረትን ነፍተው የሚጋፈጡት ጠላት ነው። ነገር ግን ልቡን በኀዘን የሚሰብረው፣ ከጀርባው ሆኖ በክህደት የሚያደማው የባንዳ ጦር ነው።

ሆኖም ሠራዊታችን “በቃኝ” ብሎ ጠብመንጃውን ጥሎ አያውቅም። ምክንያቱም የእርሱ ኪዳን ከሰዎች ግብዝነት በላይ ነው፤ ቃል ኪዳኑ ከእናት ሀገሩ ጋር፣ ከእማማ ኢትዮጵያ ጋር ነውና እስከ መጨረሻዋ የሕይወት እስትንፋስ ድረስ በፅናት ይፋለምላታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ወታደር ያለውን ጥልቅ የሀገር ፍቅር እና ጀግንነት በተመለከተ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰጡት ምስክርነት የሠራዊቱን ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

"ኢትዮጵያ በማንም ኃይል ተሸንፋ አታውቅም፤ አሁንም አትሸነፍም" በማለትም የኢትዮጵያ ሠራዊት ታሪካዊ ጀግንነት በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

ሠራዊታችን ከኢትዮጵያ ያነሰ ዓላማ የሌለው መሆኑን የሚያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ሠራዊት ዓላማው ሀገርን መከላከል እና ሰላም ማስከበር መሆኑን በአፅንኦት ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ሠራዊት "በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚጸና የድል ሠራዊት" መሆኑን በመመስከር፣ ለሀገራችን ክብር እና ሉዓላዊነት የከፈለውን ዋጋ እና ያበረከተውን ተምሳሌታዊ ገድል ያወድሳሉ።

"ለማን ልተዋት እሷን? በጣም ነው እኮ የምወዳት...ሁሌም እወድሻለሁ” የሚለው የወታደሩ ንግግርም የኢትዮጵያ ሠራዊት እውነተኛ መነሻ ሞተር ነው። ሠራዊቱ በዱር በገደሉ የሚንከራተተው፣ የሚደማው እና ሕይወቱን ለመስጠት የሚወስነው ለዝና ወይም ለሀብት አይደለም።

በየጫካው፣ በየተራራው፣ በየሸለቆው የሚንገላታው፣ በብርድ የሚቆራመደው፣ በፀሐይ የሚቃጠለው ለዚህችው ለሚወዳት፣ “እናቴ፤ እማማ” ለሚላት ሀገሩ - ለኢትዮጵያ ነው።

ኢትዮጵያን እንደ ጂኦግራፊያዊ ካርታ እና አፈር ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ደም ሥሩ፣ እንደ ሕልውናው መሠረት አድርጎ ስለሚያያት ላቡን፣ ደሙን፣ አልፎም ነፍሱን ሳይሰስት ይገብርላታል።

ወታደሩ ዛሬም ተራራውን መውጣቱን ይቀጥላል፤ ከፊቱ ያለው መንገድ ረጅም፣ ፈተናውም የበዛ ቢሆንም፣ ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር ግን በመዝገበ ቃላቱ ውስጥ የለም። "ሁሌም እወድሻለሁ፤ እጠብቅሻለሁ። መቼም... መቼም ቢሆን ተስፋ አልቆርጥም እማማ!" የሚለው የልብ ቃሉ፣ የትናንቱ፣ የዛሬው እና የነገው የኢትዮጵያ ጀግኖች የጋራ ማሕተም ነው።

ጀግናው የኢትዮጵያ ወታደር በተራራው ላይ ሲደክም እና እንደገና ሲነሣ በሚያሳየው በዚህ ትንሽ ቪዲዮ ውስጥ ታላቅ ታሪክ እየተነገረ ነው። ያ ታሪክ አንድ ጥያቄ ብቻ ይጠይቃል - “እማማን ለማን ልተዋት?” የጥያቄው መልስ ግልጽ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማንም አይተዋትም!

የኢትዮጵያ ወታደርነት መታወቂያው ይኸው ነው፤ ለእናት ሀገር ያለመሰሰት መኖር፤ ክብሯን ከፍ አድርጎ ማቆየት እና ሲያስፈልግም በክብር መሠዋት!

ለዚህም ነው እስከ ዛሬ ሀገራችን በማንም ኃይል ተሸንፋ የማውታውቀው፤ ወደ ፊትም የማትሸነፈው!

በዮናስ በድሉ

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: