Search

ተለዋዋጩ የቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ እና የኢትዮጵያ ግልጽ አቋም

ዓርብ መስከረም 29, 2019 187

ከሕንድ ውቅያኖስ እስከ ሜዲተራኒያን ባሕር የሚዘልቀው የቀይ ባሕር መስመር ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ንግድ የሚያስተናግድ የዓለም ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው ሀገራት የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዚህ መስመር ላይ የተንጠለጠለ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የቀይ ባሕር እና የአካባቢው የሥልጣኔ፣ የንግድ እንዲሁም የባሕር ኃይል ማዕከል የነበረች ታላቅ ሀገር ብትሆንም በተለያዩ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ክስተቶች ምክንያት ከባሕሩ እንድትገለል ተደርጋለች።

ይህ አጋጣሚ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትን ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የትራንዚት ወጪ፣ ለዋጋ ግሽበት፣ ለደኅንነት ስጋት እና ለኢኮኖሚ ጥገኝነት ዳርጓታል።

የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ተገጣጥሞ ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ እና ታሪካዊ የባሕር በሯን እንድታጣ መደረጉ ዛሬም ድረስ ትልቅ ሀገራዊ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ዳርቻ መራቋ በቀጣናው የታሰበውን ሰላም አላስገኘም። ይልቁንም ባለፉት ዓመታት በቀይ ባሕር እና በባብ ኤል መንደብ ዙሪያ የታየው የሁቲዎች እና የሌሎች ታጣቂ ቡድኖች መጠናከር በባሕር ዳርቻው አካባቢ ያሉ መንግሥታትን የቁጥጥር ክፍተት አጉልቶ አውጥቶታል።

እነዚህ በባሕሩ ላይ አደጋ የፈጠሩ አካላት ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን እና የሉዓላዊ ሀገራትን የደኅንነት ስሌት እስከመቀየር መድረሳቸው የቀጣናው ትልቅ ስጋት ሆኗል።

ከየመን እስከ ሶማሊያ ባለው የባሕር መስመር ላይ በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው ትስስር የቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ ደኅንነት ተነጣጥለው ሊታዩ የማይችሉ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።

የባሕር ዳርቻ ይዞታ ያላቸው የተወሰኑ ሀገራት ራሳቸው ለታጣቂዎች ከለላ በመስጠት ወይም ከውጭ ኃይሎች ጋር በመወገን የቀጣናው ስጋት ሆነው በመገኘታቸው የቀይ ባሕር ደኅንነት በዳርቻው ይዞታ ያላቸው ሀገራት ብቸኛ ኃላፊነት ነው የሚለው አግላይ መርሕ በተግባር ውድቅ ሆኗል።

በመሆኑም አሁን ያለው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለሷን አስፈላጊነት ከምንም ጊዜ በላይ አጎልቶታል።

ጥያቄው የፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሕልውና፣ የደኅንነት እና የፍትሐዊነት ጉዳይ ነው። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድ የሚከናወነው በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ-ሰላጤ መስመር በኩል በመሆኑ በቀጣናው የሚከሰት ማንኛውም የደኅንነት መስተጓጎል በቀጥታ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ይፈታተነዋል።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ባላት ሰፊ ሕዝብ፣ ጠንካራ የመንግሥት ተቋማት እና የተረጋገጠ ወታደራዊ አቅም በቀይ ባሕር የደኅንነት መዋቅር ውስጥ ድርሻ እንዲኖራት ማድረግ ቀጣናውን ከአሸባሪዎች ለመጠበቅ ወሳኝ አቅም ይፈጥራል።

ይህ የኢትዮጵያ ጥያቄ በኃይል ወይም የሌሎችን ሉዓላዊነት በመጋፋት ሳይሆን በጋራ ልማት፣ በሰጥቶ መቀበል መርሕ እና በሰላማዊ ዲፕሎማሲ ላይ የተመሠረተ ነው።

ይህን የባሕር በር አጀንዳ እውን ለማድረግ እና በቀይ ባሕር ደኅንነት ላይ ያላትን ድርሻ ለማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በተቀናጀ መንገድ መተግበር ይኖርባታል።

የደኅንነት መዋቅሩ በተጋላጭነት እና በአቅም ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በዲፕሎማሲ መሞገት ቀዳሚው ተግባር ነው።

በተጨማሪም በምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በሌሎች ቀጣናዊ ማዕቀፎች በኩል ከቀጣናው እና ከባሕረ-ሰላጤው ሀገራት እንዲሁም ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር ወሳኝ ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የታሪክ ስህተትን የማረም፣ የኢኮኖሚ ሕልውናን የማረጋገጥ እና አስተማማኝ የደኅንነት መዋቅር የመገንባት ትልቅ አጀንዳ ነው።

በቀይ ባሕር ስትራቴጂካዊ መስመር ላይ ኢትዮጵያ የሚገባትን ስፍራ እንድታገኝ የሚደረገው ጥረት፣ ለኢትዮጵያ ህልውና ብቻ ሳይሆን ለመላው የቀይ ባሕር እና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም እና ልማት ጠንካራ መሠረት የሚጥል ነው።

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: