Search

19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ዕለት ይከበራል

ዓርብ መስከረም 29, 2019 147

19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት ይከበራል።

ቀኑ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን፣ 2019 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (እንደተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሠረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ይደነግጋል።

ይህ በዓል ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበር እና ክብሯን ለማስጠበቅ ደም እና ላባቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያስከበሩት ሠንደቅ ዓላማ በጋራ የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሠንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር የመስጠት እና የማክበር ኃላፊነት እና ግዴታ አለበት።

ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ በዋናነት የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫ እና ዓርማ ነው። ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ቀን የሚከበርበት ዋና ዓላማ ለሠንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት ዜጎች የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት እና በሀገራዊ አንድነት እና ኅብረ ብሔራዊነት መግባባትን የሚፈጥሩበት ሀገራዊ በዓል በመሆኑ ነው።

ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበር ከጀመረ እነሆ 18 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት እና አስተባባሪነት በመላ ሀገራችን ወቅታዊ ሀገራዊ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በድምቀት እና በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ ይከበራል።

በዚህም መሠረት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ዕለቱን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልዕክት በማስተላለፍ በንግግር ከከፈቱ በኋላ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አማካኝነት በቀጥታ ስርጭት በመላው ሀገራችን ዜጎች በሠንደቅ ዓላማው ፊት ቃለ መሐላ የሚፈጸምበት ሥነ ሥርዓት ይፈጸማል።

ከዚያም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ማርሽ ባንድ እና ክብር ዘብ ታጅበው በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አማካኝነት ሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ይከናወናል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዐርበኞች ማኅበር እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

ይህ በዓል በመላው ሀገራችን በሚገኙ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች በተመሳሳይ ሰዓት በድምቀት እንደሚከበር ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: