Search

7ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር "ንቁ ዜጋ ደህንነቷ ለተጠበቀ ሀገር" በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር ይከበራል

ዓርብ መስከረም 29, 2019 78

7ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር "ንቁ ዜጋ ደህንነቷ ለተጠበቀ ሀገር" በሚል መሪ ቃል በተከታታይ ለአንድ ወር እንደሚከበር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ የዘንድሮውን የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በፍጥነት ማደጉን ተከትሎ በዜጎች፣ በተቋማት እና በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘረው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ለአብነትም በ2018 ዓ.ም ብቻ ከ71 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

የተቋማትንና የህብረተሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃት ማጎልበት ለጉዳዩ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፣ አካላት ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንዲችሉ በማድረግ ረገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻው ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ዋና ዳይሬክተሯ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዘንድሮው መርሃ ግብር በተለይም በህፃናት የበይነ-መረብ ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚከናወን ሲሆን፤ የፓናል ውይይቶች፣ የግንዛቤ መፍጠሪያ የሚዲያ ንቅናቄዎች እና ህብረተሰቡን ያሳተፉ የተለያዩ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

በተጨማሪም የዲጂታል 2030 ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ዝግጁነትን ማሳደግ እና የቁልፍ መሠረተ ልማት ተቋማትን የመከላከል ብቃት ማጠናከር ዋነኞቹ ተግባራት ናቸው።

ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ የመሪነት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ ሥራ ግን የሁሉም አካላት የጋራ ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም የተለያዩ ተቋማት የጥቅምት ወርን የሰራተኞቻቸውን የሳይበር ንቃት በሚያሳድግ መልኩ እንዲያከብሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የሚዲያ አካላትም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ህብረተሰቡን የማንቃትና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የሳይበር ደህንነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ23ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ የሚከበር ነው፡፡

በብርቱካን አስናቀ

#የመደመርመንግሥት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: