የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የናይጄሪያን ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማን እና ልዑካቸውን በመቀበል በከተማ አስተዳደሩ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የተመዘገቡ ስኬቶችን እና ተሞክሮዎችን ማካፈላቸውን አስታወቁ፡፡
ልዑካኑ በከተማዋ የመደመር ትውልድ ግንባታ አካል ሆነው በየሰፈሩ የተገነቡ የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራዎችን፣ የማቆያ እና እንክብካቤ ማዕከላትን፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና አገልግሎት እንዲሁም ለወላጆች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡
ጉብኝቱም በሁለቱ ወገኖች መካከል ጠቃሚ የልምድ ልውውጥ ዕድል መፍጠሩንም ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው ጠቁመዋልል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ኢንቨስትመንትን በመሠረተ ልማት ላይ ብቻ ሳያጥር በሰው ሕይወት በተለይም በሕፃናት እድገት፣ ደኅንነት እና ደስተኛነት ላይ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ይህንን መሰረት በማድረግም ፕሮግራሙ ሲጀመር 11 ብቻ የነበሩትን የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራዎች በሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ 6 ሺህ፣ እንዲሁም 20 የነበሩትን ማቆያ ማዕከላት ወደ 1 ሺህ 200 ማሳደግ መቻሉን የለውጡ ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ በተከናወኑት ስኬታማ ሥራዎች የዕድገት ውስንነት የታየባቸውን ሕፃናት መጠን ከ13 ነጥብ 5 በመቶ ወደ ቀድሞው መጠን አንድ አምስተኛ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡
አዲስ አበባን ሕፃናት ለማደግ በአፍሪካ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ያብራሩት ከንቲባ አዳነች፣ የተሻለ ትውልድ መገንባት የሥራዎቻቸው ሁሉ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም "በሕፃናት ላይ አተኩረን ስንሠራ የነገዋን ኢትዮጵያ እንገነባለን" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: