Search

የመደመር ቀይ መስመሮች፡- ከሥልጣን ምቾት ወደ ሕዝብ አገልጋይነት

ዓርብ መስከረም 29, 2019 111

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ያስተላለፉት ጥብቅ መልዕክት የኢትዮጵያን የመንግሥት አስተዳደር ባህል ከመሠረቱ የሚቀይር እና የኃላፊነትን ትርጉም የሚያድስ ታሪካዊ የፖለቲካ አቅጣጫ ነው።

በምክር ቤቱ የተደመጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ ሥልጣን የግል ክብር እና የምቾት ማካበቻ የነበረበትን አተያይ በማስወገድ በምትኩ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም የአገልጋይነት ባህልን የሚተክል ነው።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ማንሠራራት እና የሁለንተናዊ ዕድገት ምዕራፍ ውስጥ የመንግሥት ተሿሚዎች የተጣለባቸውን አደራ እንዴት መሸከም እንዳለባቸው ግልጽ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

የመንግሥት ሥልጣን ጊዜያዊ እና ለተወሰነ ተልዕኮ የሚሰጥ አደራ መሆኑን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ሥልጣን ኮፊያ እንጂ ጭንቅላት አይደለም፤ ፀሐይ ካልበረታ ወይም አስፈላጊ ካልሆነ በማንኛውም ሰዓት ሊነሣ፣ በክብር ሊቀመጥ ወይም ተሽቀንጥሮ ሊጣል የሚችል ነገር ነው" በማለት ለካቢኔ አባላቱ ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ይህ አባባል "ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል" የሚለውን ልማዳዊ እሳቤ ወደ ዘመናዊው "ሲሾም ያልሠራ ሲሻር ይቆጨዋል" መርሕ የቀየረ ትልቅ ምዕራፍ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምትፈልገው በቢሮ ተቆልፎ የሚቀመጥ እና ባለጥቁር መስታወት መኪና ውስጥ የሚደበቅ ኃላፊ ሳይሆን፣ ወደ ሕዝብ ወርዶ የሚሠራ፣ የሕዝቡን ብሶት እና ጥያቄ በአካል ተገኝቶ የሚፈታ፣ እንቅልፉን ሰውቶ ሀገርን የሚያገለግል አመራር ነው።

ሹመት የድሎት እና የእንቅልፍ ቦታ ሳይሆን የፈተና፣ የልፋት እና የትጋት ሜዳ መሆኑን አመራሩ በጥብቅ ሊገነዘበው ይገባል።

በመደመር ፍልስፍና ውስጥ የተቀመጡት የማይታለፉ ቀይ መስመሮች የመንግሥት አስተዳደርን ንጽህና ለማስጠበቅ የተዘረጉ መዋቅራዊ ድንበሮች ናቸው።

ከእነዚህም መካከል ኅሊና-ቢስነት እና ሌብነት፣ ልግመኝነት እና ስንፍና፣ እንዲሁም ወገንተኝነት እና የዘመድ-አዝማድ አሠራር ዋነኞቹ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ እንዳሰመሩበት፣ የትኛውም ሚኒስትር ወይም ከፍተኛ ተሿሚ ከተቀመጠው ሀገራዊ አቅጣጫ ውጭ የሌብነት እና የሙስና ምልክት ከታየበት በ24 ሰዓት ውስጥ ከሥልጣኑ ይነሣል።

ይህም የእጅ እና የልብ ንጽህናን የሚጠይቅ፣ አዲሱ ካቢኔ ከብልሹ አሠራር የፀዳ እና ለዜጎች ፍትሐዊ አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ሰላም እና ልማትን በተናበበ መልኩ የሚያረጋግጥ፣ ከጊዜ ጋር የሚፈጥን እና መፍትሔ ሰጪ ውሳኔዎችን የሚሰጥ አመራር ይፈልጋል።

የሕዝብን እንግልት የሚቀንሱ ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የዲጂታል አገልግሎቶች አሠራር እና የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ተጠናክረው መቀጠላቸው ለዚህ ተጨባጭ ማረጋገጫዎች ናቸው።

የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያው እና አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የመደገፉ እንቅስቃሴ የመልካም አስተዳደር እክል የሆኑ አሠራሮችን በማስወገድ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው።

ከሁሉም በላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚኒስትሮችን ሹመት ከማፅደቅ ባለፈ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ እና በተቋማቱ አፈፃፀም ላይ ጥብቅ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ድጋፍ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።

የምክር ቤቱ የቁጥጥር አቅም መጎልበት ተሿሚዎች የገቡትን ቃልኪዳን በመጠበቅ ለሕዝብ እና ለሀገር መሻት በታማኝነት እንዲሠሩ የሚያስገድድ ተቋማዊ ሚዛን ይፈጥራል።

በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የተሰጠው ኃላፊነት ከባድ ሸክምም ዕድለኝነትም ነው።

ይህንን ሀገራዊ ሸክም በጽናት ተሸክሞ የኢትዮጵያን የመጨረሻ የከፍታ መዳረሻ በማለም ሌት ተቀን የተጋ አመራር ስሙ በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቅ ቀለም ይጻፋል።

በአንፃሩ ግን የተሰጠውን ዕድል አላግባብ በመጠቀም በልግመኝነት እና በሌብነት የተዘፈቀ አመራር ዕድሉን አባክኖ ሲሻር ከመቆጨት ውጭ ሌላ ሕያው ስም ሊኖረው አይችልም።

የዚህ ዘመን አመራር መለኪያ የቃላት ድራማ ሳይሆን መሬት ላይ የወረደ እና የዜጎችን ሕይወት የለወጠ ተጨባጭ የሥራ ውጤት ብቻ ነው።

በለሚ ታደሰ

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: