ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ የሌሎችን ድንበር እና ሀብት ተመኝታ የማታውቅ፣ ነገር ግን የራሷን የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም የሕዝቦቿን ሕይወት ለማሻሻል እና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ በፅናት የምትሠራ ታላቅ ሀገር ናት።
ዛሬም በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ በስንዴ ልማት፣ በኢንዱስትሪ እና በሌሎች ዘርፎች እያስመዘገበች ያለችው አስደናቂ የስኬት ጉዞ ለወዳጆቿ ተስፋን ሲፈነጥቅ፣ ለታሪካዊ ጠላቶቿ ግን የእግር እሳት እና ከፍተኛ ስጋት ሆኖባቸዋል።
እነዚህ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የማደግ እና የማበብ መብቷን ሊቀበሉ የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች የዕድገት ጉዞዋን ለማስቆም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
በተለይም የውስጥ ተላላኪዎችን በመመልመል እና በማስታጠቅ፣ እንዲሁም በቀጣናው ያሉ ኃይሎችን የሁከት እና የጥፋት መሣሪያ በማድረግ ሀገራችንን ለማወክ እና የብልጽግና ጉዞዋን ለማስተጓጎል አሁንም ድረስ ይጥራሉ።
ነገር ግን ታሪክ የራሱ ሕያው ምሥክርነት አለው፤ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የሌላውን ግዛት ቋምጣ ባታውቅም፣ ሉዓላዊነቷን ደፍረው የመጡባትን ጠላቶች በልጆቿ ብርቱ ክንድ እና በሕዝቧ የማይናወጥ አንድነት ተመክታ ሁልጊዜም አሸናፊ ሆና መውጣቷን ዓለም ያወቀው ሐቅ ነው።
የአሁኑ ዘመን እውነታም ከዚህ የተለየ አይደለም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአሁኑ ቁመና ታላቅ ሀገርን እና የታሪክ ባለቤት የሆነውን ኩሩ ሕዝብ የሚመጥን ዘመናዊ እና አስተማማኝ አቅም ላይ ይገኛል።
ይህ ግዙፍ የጸጥታ ዝግጅት ጦርነት ለመክፈት ወይም የሌሎችን ሰላም ለማደፍረስ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የተሟላ ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ እና የሰላሟን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የተገነባ ነው።
የሀገራችን ብልጽግና እንቅልፍ የነሣቸው ኃይሎች ማንኛውንም ዓይነት ትንኮሳ ቢሰነዝሩ ሠራዊቱ ፈጣን፣ ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት በሙሉ ንቃት ላይ ይገኛል።
የአሁኑ የመከላከያ ሠራዊታችን ዝግጅት በሁሉም ዘርፎች ዘመኑን የዋጀ እና የላቀ የቴክኖሎጂ አቅም የታጠቀ ነው።
ከአፍሪካ ጠንካራ ከሆኑት ተቋማት አንዱ የሆነው የአየር ኃይላችን የዘመኑን የመጨረሻ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አደራጅቶ የኢትዮጵያን ሰማይ አስተማማኝ አድርጎታል።
ከዘመናዊ ሜካናይዝድ ክፍሎች እስከ ጠንካራ የሰማይ ነብሮች ልዩ ኃይል፣ ከሳይበር ደኅንነት እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት የመከላከያ ሥርዓት እስከ ሀገር ውስጥ የመሣሪያ እና የጥይት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ድረስ የተሟላ ቁመና ተገንብቷል።
ይህ የሠራዊታችን ዝግጅት የዓባይን የተፈጥሮ ሀብት እና የሀገር ውስጥ የልማት ተቋማትን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ስልታዊ የባሕር ላይ ጥቅሞች እና ቀጣናዊ ደኅንነት ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ የባሕር ኃይል አደረጃጀትን ያካተተ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ሠራዊቱ በአፍሪካ ቀንድ እና በአህጉሪቱ በሚኖሩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ የኢትዮጵያን የሰላም አምባሳደርነት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
በአጠቃላይ ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ በግብርናውና በሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር አሻራውን የሚያሳርፍ፣ በችግር ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስከብር እውነተኛ የሕዝብ ጋሻ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: