Search

የኢትዮጵያዊ ሥልጣኔ ብሥራት፦ በራስ አቅም እና ዕሴት ላይ የሚገነባ የብልጽግና ጉዞ

ዓርብ መስከረም 29, 2019 78

በዓለም ታሪክ ውስጥ ታላላቅ ሥልጣኔዎችን መገንባት የቻሉ ማኅበረሰቦች ለደረሱበት የዕድገት እና የብልጽግና ማማ በዋናነት መነሻ ያደረጉት የራሳቸውን ማኅበራዊ ዕሴት፣ ባህል እና ዕሳቤ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ማብራሪያቸው ላይ በግልጽ እንዳስገነዘቡት የአውሮፓ እና የምሥራቅ እስያ ሕዝቦች ላስመዘገቡት ፈጣን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ዕድገት ዋነኛው ምስጢር ለውጡን በራሳቸው የማኅበረሰብ መሠረት ላይ መገንባታቸው ነው።

እነዚህ የሠለጠኑ ዓለማት ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን እና ጠቃሚ ግብዓቶችን ቢወስዱም በቀጥታ ከመገልበጥ ይልቅ ከራሳቸው ነባራዊ አውድ እና ዕሴት ጋር በማጣመር ስኬታማ መሆን ችለዋል።

ኢትዮጵያም በተመሳሳይ መርህ የውጭ ጥገኝነትን በማስወገድ የራሷን ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔ በመገንባት ላይ እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስምረውበታል።

ይህን ታላቅ ራዕይ እውን ለማድረግ ደግሞ በራስ አቅም የመቆም አስተሳሰብ እና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ፣ ታሪካዊ ቅርስ እና አምራች የሰው ኃይል በሚገባ ጥቅም ላይ በማዋል የልማት እና የዕድገት ጉዟችንን በራሳችን ዜጎች መምራት ግድ ይላል።

ይህ ተግባራዊ መርሕ ረቂቅ ጽንሰ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በስንዴ ልማት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች እንዲሁም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ፍሬ እያፈራ ያለ ተጨባጭ እውነት ሆኗል።

ወቅታዊም ሆነ ዘላቂ ተግዳሮቶች አስተማማኝ መፍትሔ የሚያገኙት ከውጭ በሚመጡ የተቀዱ ሀሳቦች ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን አውድ እና ታሪክ መሠረት ባደረጉ መፍትሔዎች ብቻ ነው።

ስለሆነም ለገጠሙን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ችግሮች ኢትዮጵያዊ መፍትሔ የመፈለግ ባህልን ይበልጥ ማዳበር ያስፈልጋል።

ይህንን ብሔራዊ ትልም ዳር ለማድረስ ሀገራዊ ፍቅር ያለው፣ በማንነቱ እና በባህሉ የሚኮራ፣ እንዲሁም ችግሮችን በውይይት እና በሀገራዊ ዕውቀት ለመፍታት የሚተጋ አዲስ ትውልድ መገንባት የሁሉም ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት።

እንዲህ ዓይነቱ ትውልድ ለሰላም፣ ለልማት እና ለአንድነት ዘብ በመሆን ኢትዮጵያን ወደ አዲሱ የሥልጣኔ ምዕራፍ ያሻግራታል።

በሃና ምንዳሁን

#የመደመርመንግሥት

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: