የሕንድ እና አፍሪካ የረጅም ዘመን ትብብር በሕንድ “ቪክሲት 2047” ርዕይ እና በአፍሪካ ኅብረት “አጀንዳ 2063” መካከል በሚደረግ ቅንጅት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር (ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በሕንድ-አፍሪካ ትብብር ላይ ያተኮረ መድረክ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አዘጋጅቷል።
በመድረኩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ ኢድሪስን ጨምሮ አምባሳደሮች እና የዘርፉ ምሁራን የተገኙ ሲሆን የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር (ዶ/ር) ንግግር አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ እና የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት፣ የሰብዓዊ ክብር፣ የሉዓላዊነት እና በራስ አቅም የመወሰን ታሪካዊ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕንድ እና አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች ሳቢያ ተመሳሳይ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ያወሱት ሚኒስትሩ፣ የሕንድ ውቅያኖስ የሁለቱን ወገኖች የሕዝብ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ትሥሥር የሚያሳልጥ ዘመን ተሻጋሪ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በደቡባዊ ክፍለ ዓለም ማዕቀፍ የአፍሪካ እና የሕንድ የንግድ ግንኙነት በመሠረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በቴሌኮም ዘርፎች ይበልጥ ሊጎልብት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ እና በሕንድ መካከል ያለው የንግድ ትሥሥር ከአክሱማዊት ሥልጣኔ እና ከአዱሊስ ወደብ ንግድ የሚመነጭ ታሪካዊ መሠረት ያለው መሆኑን ያመላከቱት ዶክተር ጃይሻንካር፣ በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መሪነት የሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት በፍጥነት እየተሸጋገረ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ600 በላይ የሕንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርተው ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመው በኢነርጂ፣ በግብርና፣ በሕክምና መገልገያ እና መድኃኒት እንዲሁም በስኳር ፕሮጀክቶች በጋራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ሁለቱ ሀገራት በብሪክስ (BRICS) እና በአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች ላይ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
#የመደመርመንግሥት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: