ዓለም አራት ታላላቅ የኢንዱስትሪ አብዮቶችን አስተናግዳ አምስተኛውን ለመቀበል በደጅ ትገኛለች።
በእነዚህ የታሪክ ምዕራፎች ራሳቸውን ያዘጋጁ መንግሥታት ዓለም አቀፍ የበላይነትን ሲይዙ፣ ዝግጁ ያልነበሩት ግን የአብዮቶቹ ትራፊ ተቋዳሽ አሊያም የኃያላኑ ተከታይ ለመሆን ተገድደዋል።
የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ አብዮት በእንፋሎት ሞተር እና በማኑፋክቸሪንግ ዓለምን ሲለውጥ፣ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት የሥልጣን ሽኩቻ እና የውስጥ ክፍፍል ውስጥ ተዘፍቃ ነበር።
ሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በኤሌክትሪክ እና በጅምላ ምርት አቅምን ሲገነባም ኢትዮጵያ ዘመኑን ባለመዋጀቷ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች።
"በትግራይ ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር? በጎንደር ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር? በአሰብ ቢመጣ መቼ ይገባ ነበር? በሰማይ መጣ እንጂ በማናውቀው ሀገር" የሚለው የአርበኞች አባቶቻችን የቁጭት ግጥም፣ በወቅቱ የነበረውን የቴክኖሎጂ ዝግጅት ማጣት እና ያስከተለውን የሉዓላዊነት አደጋ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ሦስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በተከሰተበት ወቅትም ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ በመሆኗ ዕድሉን ሳትጠቀምበት አልፋለች።
የየወቅቱ የፖለቲካ ሊሂቃን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እና እሴት ያላገናዘቡ የባሕር ማዶ ርዕዮተ ዓለሞችን በግድ ለመጫን መሞከራቸው፣ እንዲሁም አቅምን ወደ ልማት ከመቀየር ይልቅ ለእርስ በርስ ግጭት ማባከናቸው ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ የዕድገት ዑደቶች አርቋት ቆይቷል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ግን በመደመር እሳቤ ኢትዮጵያ በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን ሰፋፊ መሠረቶች ተጥለዋል።
ባለፉት የኢንዱስትሪ አብዮቶች ታላላቅ ሥልጣኔዎች እንደተገነቡት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የራሷን የዘመናት ታሪክ እና ማኅበራዊ ወረት መሠረት በማድረግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ጥበቦችን ከነባር እሴቷ ጋር አጣጥማ መጓዝ ጀምራለች።
ይህ አካሄድም ኢትዮጵያን ከገባችበት የኋላቀርነት አረንቋ ፈጥኖ ለማውጣት ብርቱ መፍትሔ እየሆነ መጥቷል።
በተግባርም የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን ቀርጾ በመተግበር የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የምርምር ማዕከላትን በመገንባት፣ እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው።
የዜጎችን ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚያሳልጠው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ያረጋገጡት የቴሌብር እና ሌሎች የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች ኢትዮጵያን ለዘመነኛው የቴክኖሎጂ አብዮት ብቁ እያደረጓት ይገኛሉ። እነዚህ የዲጂታል መድረኮች ነገን ለመዋጀት የሚያስችሉ ጽኑ መሠረቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መጽሐፋቸው "ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት መላመድ እና ጥቅም ላይ ማዋል ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፤ ይህም ዳቦ ከማስገኘት ባሻገር በላቀ ደረጃ የኢኮኖሚያዊ መዋቅር ሽግግርን ያፋጥናል፤ ከመጪው ጊዜ ጋርም እኩል ተራማጅ ያደርገናል" ይላሉ፡፡ ይህ ሐሳብ በተቃኙ ስትራቴጂዎች ታግዞ በስኬት እየተተረጎመ ይገኛል።
በቀጣዮቹ ዓመታትም ኢትዮጵያ እነዚህን ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች አጠናክራ በመቀጠል በቴክኖሎጂው ዘርፍ ፊታውራሪ ለመሆን በጽኑ እየሠራች ትገኛለች።
በዓይናለም ሃድራ
#የመደመርመንግሥት
#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: