ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባካሄደቻቸው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውስጥ የማዕድን ዘርፍ ከቀድሞው አነስተኛ አስተዋጽኦ ወጥቶ የሀገርን ኢኮኖሚ ከሥረ-መሠረቱ ሊለውጥ የሚችል ወሳኝ የዕድገት ምሰሶ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ከዚህ ቀደም ሀገራችን በግብርና ምርቶች ላይ ብቻ የነበራትን የውጭ ምንዛሪ ጥገኝነት ለመቀነስ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የኢንዱስትሪ መሠረትን ለማስፋት የማዕድን ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም አስፈላጊነት ከምንጊዜውም በላይ ጎልቶ ወጥቷል።
የማዕድን ዘርፉን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር መንግሥት በርካታ መዋቅራዊና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጓል።
በዚህም የዘርፉን ኢንቨስትመንት የሚስቡ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ድንጋጌዎች ወጥተዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የታሪፍና የታክስ ማሻሻያዎች፣ የካፒታል ፈቃድ ማቃለልና ፈጣን ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ተዘርግቷል። የባህላዊ ማዕድን አውጪዎችን በህጋዊ መንገድ በማደራጀት፣ የቴክኒክና የበጀት ድጋፍ በማድረግ ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ምድር በከበሩ እና በኢንዱስትሪ ማዕድናት የበለፀገ ነው። እነዚህ ማዕድናት ለሀገር ኢኮኖሚ በርካታ ጥቅሞችን ያስገኛሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከባህላዊና ዘመናዊ አምራቾች በዓለም ገበያ ዋጋ ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ በመግዛት የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማሳደግ እየተጠቀመበት ይገኛል።
የማዕድን አሰሳና ማውጣት ሥራዎች ለብዙ ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በላይ፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሚደረጉ ሽርክናዎች አማካይነት ዘመናዊ የማዕድን ቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ያስችላሉ።
ማዕድናትን በጥሬው ወደ ውጭ መላክ የሀገርን ሀብት በርካሽ የመሸጥ ያህል ነው። በመሆኑም የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ያለው አስተዋጽኦ የሚረጋገጠው እሴት በመጨመር ነው።
ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ወርቅን፣ ታንታለምንና ሊቲየምን በሀገር ውስጥ በማቀነባበርና በማንጻት የተጠናቀቁ ወይም አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፉ ምርቶች ማድረግ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እየተሠራበት ይገኛል።
የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ ሲደገፉ፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ የጥሬ ዕቃ ዋጋ መዋዥቅና የዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ የሚደርስባትን ተፅዕኖ ለመቋቋም አቅም ታገኛለች።
በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ከጥሬ ዕቃ ምንጭነት አልፎ የሀገር ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት፣ የኢንዱስትሪ መያዣና የትውልድ ተሻጋሪ ብልጽግና ብርቱ ምሰሶ የመሆን ሙሉ አቅም አለው።
ይህ አቅም እውን ሊሆን የሚችለው ግልጽ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመከተል፣ በሀገር ውስጥ እሴት የመጨመር አቅምን በማሳደግ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመተግበርና አካባቢን መሠረት ያደረገ ዘላቂ አሠራርን በማረጋገጥ ብቻ ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግም የመደመር መንግሥት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: