በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በይፋ ሥራ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፋብሪካው ሥራ መጀመሩን ሳበስር በታላቅ ደስታ ነው ሲሉ ገልጸው፣ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር ከፍተኛ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
ይህ የማጣሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣ የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከር እና ሀገራችንን በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
አክለውም ይህ ውጥን ሀገራዊ ሀብቶችን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይበልጥ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አስምረውበታል።
ኢትዮጵያ ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ ባለው የልማት ሂደት በሀገር ውስጥ የላቀ እሴት እየፈጠረች እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: