የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው ዕለት የከተማ አስተዳደሩ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ከገባነው ቃል በላይ በመፈጸም ያስመዘገብነውን ስኬት መነሻ በማድረግ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከበፊቱ የላቀ ውጤት ለማምጣት የ5 ዓመት እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ አዘጋጅተን የላቀ ለውጥ ለማምጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የሥራችን ስኬት የሚመዘነው በተሠሩ ሥራዎች ብዛት ብቻ አይደለም፤ ዋናው መመዘኛ የሕዝባችንን የኑሮ ጫና ምን ያህል እያቀለልን ነው፣ አገልግሎቶችን ምን ያህል አሻሽለናል፣ ለወደፊትስ የሚቀጥል ምን ዓይነት ተቋማዊ አቅም ገንብተናል የሚለው ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
የመደመር መንግሥት እንደ መሆናችን የተቋማትን፣ የሀብቶችንና የእውቀትን አቅም በማቀናጀት፣ የዛሬን ውጤት ወደ ነገ አቅም፣ የዛሬን ስኬት ወደ ዘላቂ ብሔራዊ ብቃት እየቀየርን የጋራ ሀገር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን ብለዋል።
አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ከተሞች ምሳሌ፣ ከዓለም ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ለሕዝቧ የተሻለ ኑሮ የምታረጋግጥ ከተማ መሆን እንዳለባት ያመላከቱት ከንቲባ አዳነች፣ ይህም የሚረጋገጠው በተቀናጀ አመራር፣ በጠንካራ ተቋማትና በሰው ተኮር አፈጻጸም መሆኑን አመልክተዋል።
የዛሬ ሥራችን የነገ አቅማችን ነው፤ የዛሬ ውጤታችን የነገ የኢትዮዽያ ሥልጣኔ መሠረት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: