ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 5 እና 10 ዓመታት ውስጥ በጥሬ ዕቃ መልክ የምትልካቸውን ምርቶች እሴት በመጨመር በመተካት፣ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ልምዷን በደረጃ እንደምትገታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና ሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት አጋርነት የተቋቋመውን ይህን የማጣሪያ ፋብሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የመደመር ስትራቴጂ ዋና ዓላማ ሀገራችን ጥሬ ዕቃዎችን በአነስተኛ ዋጋ ልካ መልሳ በውድ ዋጋ የተዘጋጁ ምርቶችን የመግዛት አሠራርን ለማስቀረት ነው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ጥጥ፣ ቡና እና ወርቅ የመሳሰሉ ጥሬ ዕቃዎችን በዝቅተኛ ዋጋ ከላከች በኋላ፣ ተሰናድተው ወደ አፍሪካ ገበያ በብዙ እጥፍ ዋጋ ተመልሰው እንደሚሸጡ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለአብነትም በአዲስ አበባ በ8 ዶላር የሚሸጥ ቡና ውጭ ሀገር ተቆልቶና ተዘጋጅቶ በስታር ባክስ ከ30 ዶላር በላይ፣ በጣሊያን ደግሞ ወደ እስፕሬሶ ተለውጦ እስከ 50 ዩሮ እንደሚሸጥ ጠቅሰዋል።
ይህ አሠራር በወርቅ ብቻ ሳይሆን በማዳበሪያ እና በሌሎች ቁልፍ ዘርፎችም ተተግብሮ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ነው ያብራሩት።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: