Search

በአዳም ረታ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ንባብ ያቀረበው 'የጥበብ ቃሊም' ሥነ-አዳም መጽሐፍ ተመረቀ

ቅዳሜ መስከረም 30, 2019 85

በአዳም ረታ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ንባብ የተደረገበትና 'የጥበብ ቃሊም' ሥነ-አዳም የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ በወ-መዘክር አዳራሽ በይፋ ተመረቀ።

በትዕግስት ሳሙኤል እና በቢኒያም አቡራ በጋራ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ፤ ደራሲ አዳም ረታ ከ'ማሕሌት' እስከ 'አፍ' የጻፈበትን ዐውድ እና የተጠቀመበትን ልዩ የአጻጻፍ ዘዴ ከተለያዩ አንጻሮች የሚተረጉምና የሚተነትን ነው።

ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ድረ-ገጾቻቸው በአዳም ረታ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ዕይታዎቻቸውን በማጋራት የሚታወቁት ሁለቱ ደራሲያን፤ ተመሳሳይ የንባብ ባህል እንዳቀራረባቸው እና በተለይም በአዳም ረታ ሥራዎች ላይ የሚቀርቡ የተራራቁ ምልከታዎች ይህን መጽሐፍ በአንድነት እንዲያበረክቱ እንዳነሳሳቸው ለኢቲቪ መዝናኛ ገልጸዋል።

ደራሲያኑ አዳም ረታ በልቦለዶቹ ሁሉንም የጥበብ ዘርፎች የሚዳስስ በመሆኑ፣ የተለያዩ የጥበብ ዕውቀቶችና ቅኔዎች በአንድነት የሚፈሱበት ማዕከል መሆን በመቻሉ ልክ እንደ ወንዝ ጥግ በመሆኑ መጽሐፉን 'የጥበብ ቃሊም' ብለው እንደሰየሙት ተናግረዋል።

መጽሐፉ የአዳም ረታን ሥራዎች በሩቅም ሆነ በጥልቅ ለሚያውቁ በሚሆን መንገድ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ጨርሶ አንብበው ለማያውቁትም ለንባብ የሚያነሳሳ፣ ለሥነ-ጽሑፍ ወዳጆች የአጻጻፍ ዘዴና ብልሃትን የሚያስተምር እንዲሁም አዳምን በተለየ አንጻር ለሚረዱት ለውይይትና ለተጨማሪ ጽሑፍ የሚጋብዝ ሆኖ መቅረቡን ገልጸዋል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከታደሙ የኪነ-ጥበብ ሰዎች አንዱ የሆነው ደራሲ ተስፋዬ ማሞ በሰጠው አስተያየት፤ "ይህ መጽሐፍ የአዳም ረታን ሥራዎች መረዳት ለከበደው አንባቢ የተለያዩ መንገዶችን የሚያሳይ መነጽር ነው" በማለት በጋራ የተጻፈ ሂሳዊ ንባብ መሆኑ ሌላው ጠንካራ ጎኑ እንደሆነ ጠቅሷል።

ደራሲ ቢኒያም አቡራ ከዚህ ቀደም 'ባለቅኔዋ ሶሪት'፣ 'ወደ ፍቅር ጉዞ' እና በግጥም (አሰናኝነት) 'ሃያ ሦስት' የሚሉ የድርሰት ሥራዎችን ያስነበበ ሲሆን፤ ደራሲ ትዕግስት ሳሙኤልም በእንግሊዘኛ የተጻፉትን 'A Walk To Be Cherished' እና 'The Chronicles Of The Unseen and Other Stories' እንዲሁም በአማርኛ የቀረበውን 'ዓይነ ርግብ' የተሰኙ መጻሕፍትን ለንባብ ማብቃቷ ይታወሳል።

10 ምዕራፎች እንዲሁም 302 ገጾች ያሉት 'የጥበብ ቃሊም' መጽሐፍ በ600 ብር ለገበያ ቀርቧል።

 

በአክሱማዊት ገብረሕይወት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: