የዘመናዊ ተዋጊ ጄቶቻችን የሞተር ድምፅ ሰማዩን ሰንጥቆ ሲያስተጋባ የሚሰማው ጩኸት ብቻ ሳይሆን፣ የጠላትን አከርካሪ የሚሰብር እና የማይደፈረውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያበስር የጀግንነት ነጎድጓድ ነው፡፡
"ሰማዩ የኛ ነው!" የሚለው የአየር ኃይላችን መሪ ቃል በቆራጥ አብራሪዎቻችን ልብ ውስጥ በደማቁ የተጻፈ የሕልውናችን ማኅተም ነው፡፡
አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሌት ተቀን የማይተኛ የሀገር ዋስትና፣ የሕዝብ ኩራት እና የማይበገር የብረት ጋሻ በመሆን ኢትዮጵያን በክፋት ዓይን የሚያይ ማንኛውንም ታሪካዊ ጠላት ለማንበርከክ፣ ይህ የሰማይ ላይ ንስር ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈሪ ቁመናን ተላብሶ በተጠንቀቅ ቆሟል፡፡
አየር ኃይላችን አንድ ክፍለ ዘመን ሊደፍን በተቃረበው የጀግንነት ታሪኩ የሀገርን ክብር በማስጠበቅ ረገድ የማይተካ አኩሪ ገድል ፈጽሟል፡፡
በ1969 ዓ.ም በዚያድ ባሬ ወረራ ወቅት የጠላትን ሚግ-17 እና ሚግ-21 የጦር አውሮፕላኖች በኤፍ-5ኢ ጄቶቹ እንደ ቅጠል በማርገፍ ፍጹም የበላይነቱን ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡
ጄኔራል ለገሰ ተፈራ፣ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ፣ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እና ሌሎችም ጀግኖች የጠላትን ቅዠት በአየር ላይ በማክሸፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በሻዕቢያ ወረራ ወቅትም፣ የኢትዮጵያ ሱ-27 ተዋጊዎች የጠላትን ሚግ-29 አውሮፕላኖች ከጥቅም ውጭ በማድረግ እንደ ጉም አትነነውታል፡፡
ይህ ድል ይበልጥ የሚያኮራው ተቋሙ በ1983 ዓ.ም ከገጠመው ከባድ መዋቅራዊ መፍረስ እና ፈተና በፍጥነት አገግሞ ጀግኖች አብራሪዎቹ ግላዊ በደላቸውን ወደ ጎን በመተው ለሀገራቸው ቀዳሚ በመሆናቸው ነው፡፡
ዛሬ ላይ አየር ኃይሉ አቅሙን በማጠናከር ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ ሁለገብ ተዋጊ ጄቶችን፣ የላቁ የውጊያ እና የማሰልጠኛ አውሮፕላኖችን ታጥቆ አየር ክልላችንን በንቃት እየጠበቀ ይገኛል፡፡
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ራስን የመቻል ስትራቴጂን በመተግበሯ የተገነቡት "ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ" እና "ኤይሮ አባይ" የተሰኙ የድሮን ማምረቻ ማዕከላት ለቅኝት፣ ለመረጃ ማሰባሰብ እና የታለመ ዒላማን በከፍተኛ ትክክለኛነት በመምታት የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ስምሪት የሚያከሽፉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በማምረት ኢትዮጵያን ከገዢነት ወደ ቴክኖሎጂ አምራችነት በፍጥነት አሸጋግረዋታል፡፡
ይህ የቴክኖሎጂ፣ የመሠረተ ልማት እና የሰው ኃይል ግንባታ ታሪካዊ ተገዳዳሪዎቻችንን በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የከተተ የማይነቃነቅ የደኅንነት ጋሻችን ሆኗል፡፡
አሁን ላይ ሉዓላዊነታችንን የሚዳፈሩ ኃይሎች በዝምታ የሚታለፉ ሳይሆኑ በሰማይም ሆነ በምድር ታድነው የማያዳግም እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጠላትን አከርካሪ ሰብሮ ሀገርን የሚያስከብር፣ የምሥራቅ አፍሪካን ሚዛን የጠበቀ እና የኢትዮጵያን ደህንነት የሚያረጋግጥ የዘመናችን የቴክኖሎጂ ማማ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰማይ በታመኑ የብረት ክንፎች ጥበቃ ሥር ነው፤ ሀገራችንም በጀግናው አየር ኃይሏ ዋስትናነት ለዘላለም ተከብራ ትኖራለች!
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: