የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በታሪክ ውጣ ውረድ እና በዘመናት ፈተናዎች ውስጥ አልፎ የጸና የሕዝብ መከታ፣ የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ ጠበቃ እና የኢትዮጵያ የመጨረሻው ምሽግ ሆኖ ቀጥሏል።
በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ታሪካዊ ተልዕኮ በላቀ ብቃት እና በጽኑ ዲሲፕሊን እየተወጣ የሚገኘው ይህ ሠራዊት፣ የአንድ ወገን ወይም የቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ሕልውና መጠበቂያ ምሰሶ ነው።
ወታደሩ ለሕዝቡ እና ለኢትዮጵያ ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ በመሆኑ፣ ከዚህ ውጪ ያለ ማንኛውም መሥዋዕትነት ለእርሱ ቀላሉ መንገድ ነው።
የሀገር ፍቅር ሲባል ዐሥር ሞት ቢኖር ዐሥር ጊዜ ለመሞት የሚያስደፍር ጥልቅ መንፈሳዊ ቁርኝት እንደሆነ የሚያስመሰክረው ይህ ተቋም እና አባላቱ ብቻ ናቸው፡፡ የወገንን ሰላም እና የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ዘላቂነት በመጠበቅ ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ወታደር በግሉ ማንም ላይ ቂም እና በቀል የለውም፤ የሠራዊቱ ደመኛ ጠላት ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ለማፍረስ፣ ሰላሟን ለማደፍረስ እና ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር የሚሰለፍ የውስጥ እና የውጭ የጥፋት ኃይል ብቻ ነው።
ወታደርነት በውል እና በደመወዝ የሚለካ ሙያዊ ስምሪት ብቻ ሳይሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቅዱስ አደራ በመሆኑ፣ ሠራዊቱ የግል ቂም ሳይኖረው ሀገራዊ ስጋቶችን ብቻ ለይቶ የመመከት መርሕን ይከተላል።
በዚህም ምክንያት የሠራዊቱ ግብ በግለሰቦች ላይ የተቃጣ ቂም ሳይሆን የኢትዮጵያን ዘላቂ ሕልውና ማረጋገጥ እና የሕዝቦቿን ደኅንነት ማስጠበቅ ነው።
ኢትዮጵያ የሌሎችን መሬት የመውረር ወይም ጥቃት የመክፈት ፍላጎት የሌላት እና የሰላም ዘብ የሆነች ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ ሠራዊቷም ጥይት የሚተኩሰው የኢትዮጵያ ሕልውና አደጋ ላይ መውደቁን አረጋግጦ የመጨረሻ ውሳኔ ሲወስን ብቻ ነው።
ሆኖም የኢትዮጵያን ትዕግሥት እንደ ድክመት በመቁጥር ሉዓላዊነቷን የሚዳፈር እና ሰላሟን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ጠላት የእሳት አሎሎ የሆነውን የዚህን ጀግና ሠራዊት ክንድ ይቀምሳል።
በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም፣ በጥናት በተደገፈ ሥልጠና እና በላቀ የውጊያ ዝግጁነት የታነጸው የመከላከያ ኃይል፣ ሀገራዊ ደኅንነትን ለማስከበር እና የጥፋት ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ ዘወትር በተሟላ ቁመና ላይ ይገኛል።
ይህ የብረት ክንድ ያለው ሠራዊት በአውደ ውጊያ ላይ የሚያሳየው ቆራጥነት ያህል፣ ከውጊያ በኋላ የሚያሳየው ሰብዓዊነትም የዚሁ ታላቅ ሕዝብ ነጸብራቅ ነው።
የኢትዮጵያ ወታደር ሰብዓዊነት ከአንጀት ከተሸመነው የኢትዮጵያዊነት ልብ የተወረሰ የሞራል የበላይነት መግለጫ ነው።
በእጁ የወደቁ እና ሊያፈርሱት የተኮሱበትን ጠላቶች እንኳን ከበቀል ይልቅ በወንድምነት እና የእናት ያህል በሆነ ጥልቅ እንክብካቤ ቁስላቸውን የሚያክም፣ ደማቸውን የሚጠርግ እና ሕይወታቸውን የሚያድን የሕግ እና የሞራል የበላይነት ያለው ሠራዊት ነው።
ይህም የኢትዮጵያ ሠራዊት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች እና የጦርነት ሕጎች ባለፈ፣ ከጥንት አባቶች ሲወርድ ሲወረድ የመጣውን የመንፈስ ልዕልና የሚያሳይ ምስክር ነው።
በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ ትጥቅ እና በስትራቴጂያዊ ዝግጁነት ራሱን እያደሰ የመጣው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ሀገራዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት የመጨረሻው ምሽግነቱን በተግባር አረጋግጧል።
በዲሲፕሊን የታነጸው፣ በሕዝብ ፍቅር የታሸው እና በሰብዓዊነት ራስ ላይ የተቀመጠው ይህ ሠራዊት፣ የትኛውንም ፈተና በመቋቋም የኢትዮጵያን ሰማይ እና ምድር አስተማማኝ የሰላም አየር እንዲተነፍሱ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን በጽናት መወጣቱን ይቀጥላል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: