Search

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያረጋግጠው አዲስ የሥልጣኔ ምዕራፍ

እሑድ ጥቅምት 01, 2019 82

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር ከቃላት ባሻገር በተግባር የተፈተነ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አቅጣጫን የሚያበስር ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

በታሪክ ሂደት ውስጥ ዓለምን የለወጡ ታላላቅ ራዕዮች ሁሉ መጀመሪያ ላይ በጥርጣሬ እና በተሳልቆ መታየታቸው አልቀረም፤ የአሁኑ የኢትዮጵያ ጉዞም የዚህ ማረጋገጫ ነው።

ዛሬ ላይ ግን ተስፋን ብቻ ይዞ ከመጠበቅ ይልቅ አቅዶ የሚተገብር፣ የተቺዎችን ድምፅ በግዙፍ ሥራዎች የሚመልስ ብቁ አቅም እና ጽኑ አቋም ያለው አመራር እየተፈጠረ ነው።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀየሰው የበጋ ስንዴ ልማት ሀገራችንን ከጥገኝነት ማዕቀፍ በማውጣት ራሷን እንድትችል መንገድ መጥረጉ አንዱ ማረጋገጫ ነው።

የከተሞች ኮሪደር ልማትና መሰረተ ልማትን የማዘመን ሥራዎች የነበሩትን ፈተናዎች በስኬት አልፈው የከተሞቻችንን ገጽታ ከመቀየር አልፎ የአህጉራችን መነጋገሪያ ለመሆን በቅተዋል።

ለዘመናት ቆመው የነበሩ እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ መገጭ፣ ርብ እና ጣና በለስ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ምርት እና አገልግሎት መሸጋገራቸው መንግሥት የታለሙ ተስፋዎችን ወደ ተጨባጭ ብሔራዊ ሀብት የመቀየር የአስፈጻሚነት ብቃት እየገነባ መምጣቱን ያሳያል።

ከጂኦፖለቲካ አንጻር ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው በሚል በባለጋራዎችና በተስፋ ቆራጮች ይነዛ የነበረው አፍራሽ ትረካ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል።

ዛሬ ኢትዮጵያ የመፍረስ ስጋት ያለባት ሳትሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እንደ ዋና ማዕከል (Anchor State) በመቆም ቀጣናዊ መረጋጋትንና ልማትን የምትመራ፣ በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን የሚያስከብር ጠንካራ ብሔራዊ አቋም የገነባች ኃይል ሆና ወጥታለች።

ይህ የጂኦፖለቲካዊ ሚዛን ለውጥም ታሪካዊ ባላንጣዎቻችን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የነበራቸውን ተስፋ አስቆርጦ ወደ መከላከል እና ስጋት እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል።

በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ረገድ ደግሞ የመደመር ፍልስፍና ዋና አካል የሆነው አካታችነት እና የትብብር ፖለቲካ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎችን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በማሳተፍ፣ ዜጎችን በደረጃ ከመመደብ አስተሳሰብ መውጣት መቻሉ ለፖለቲካዊ ሰላም ታላቅ መሠረት ጥሏል።

በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሀሳቦች ላይ ተመስርቶ የሚደረገው የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በፉክክር እና በትብብር ሚዛን ላይ በመገንባት የሕግ የበላይነትን እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንግግር ያስተላለፈው ዋና መልዕክት፣ ኢትዮጵያ የነገ ዕጣ ፈንታዋን በራሷ እጅ ለመጻፍ መቁረጧን ነው።

በኅብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና በሥነ-ምኅዳር ጥበቃ ላይ የተመሰረተው አዲሱ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው የተስፋ አድማስ እና ኩሩ ታሪክ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።

#የመደመርመንግሥት

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: