Search

የሰንደቅ ዓላማችን ክብር፡ የሉዓላዊነት፣ የጽኑ ኅብረት እና የትውልዶች ዐሻራ

ሰኞ ጥቅምት 02, 2019 94

‎ከፍ ብሎ በሰማያችን ሥር ሲውለበልብ የምናየው የሦስቱ ቀለማት ሕብረት ተራ ጨርቅ አይደለም፤ የትውልዶች መስዋዕትነት፣ የነፃነት አየር እና የብሔራዊ ኩራታችን ሕያው ምስክር እንጂ።

ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ማኅተም፣ የቃል ኪዳናችን ምልክት እና የማንነታችን ሕያው ጥላ ነው። ዘመናትን የተሻገረው ይህ ታላቅ ክብር፣ የኢትዮጵያውያንን የነፃነት ታሪክ እና የጋራ ዕጣ ፈንታ በአንድነት ያስረዘመ ታላቅ ሀገራዊ አደራ ነው። ይህንን የጋራ እሴት መነሻ በማድረግ በብሔራዊ ደረጃ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን፣ የጋራ ማንነታችንን የምናድስበት እና የኢትዮጵያን ከፍታ ዳግም የምናረጋግጥበት ልዩ ዕለት ነው። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትና የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ የተደነገገው ይህ ክብር በቀላል ስዕል የተሰናዱ ሕብረ-ቀለማት ስብስብ አይደለም። አረንጓዴው የኢትዮጵያ ለምለምነት፣ የሥራ እና የልማት ማሳያ ሲሆን፤ ቢጫው የተስፋችን፣ የፍትሕ እና የእኩልነታችን ብርሃን ነው፡፡ ቀዩ ደግሞ ለኢትዮጵያ ነፃነት እና ሉዓላዊነት ሲባል የፈሰሰው የጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን ንጹህ ደም መታሰቢያ ነው። በታሪካችን ውስጥ ያጋጠሙንን በርካታ ፈተናዎች፣ መከራዎች እና ውጣ ውረዶች ተሻግረን ዛሬ ላይ የቆምነው በዚህ የጋራ መጠለያችን ሥር ባለን ጽኑ ኅብረት ነው። ሰንደቅ ዓላማችን የብሔር፣ የሃይማኖት እና የቋንቋ ልዩነቶቻችንን አዋህዶ በአንድነት የሚያቆመን የታላቋ ኢትዮጵያ መጠለያ ጥላ ነው። ዛሬ በየአቅጣጫው የምናስመዘግባቸው የልማት፣ የኢኮኖሚ እና የመሰረተ ልማት ዕድገቶች ሁሉ ግባቸው የዚችን ታላቅ ሀገር ባንዲራ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ ማሣየት ነው። ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ እስከ ኮሪደር ልማት፣ ከግብርና አብዮት እስከ ቴክኖሎጂ ሽግግር የምናደርጋቸው የትግል ጉዞዎች ሁሉ የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር የሚያስጠብቁ የዛሬው ትውልድ አሻራዎች ናቸው። ይህንን ዕለት ስናከብር በቀለማቱ ሥር ቆመን የጋራ ሀገራችንን ሰላም፣ ልማት እና ዕድገት ለማረጋገጥ ዳግም ቃል እንገባለን። ይበልጥ የተሳሰረች፣ የበለጸገች እና ለዜጎቿ ሁሉ እኩል ተስፋ የምትሰጥ ኢትዮጵያን የመገንባት ሀገራዊ ኃላፊነታችንን እናድሳለን። #የመደመርመንግሥት በሔዋን ጌታቸው

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: