Search

ሠንደቅ ዓላማችን የመደመር ዕሴታችን፣ የአንድነታችንና የኢትዮጵያ ከፍታ ምልክታችን ነው”፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ሰኞ ጥቅምት 02, 2019 143

ሠንደቅ ዓላማ የቀደምት አባቶችን የመሥዋዕትነት ታሪክ የሚያስታውስ፣ የዛሬን ትጋት የሚያንፀባርቅና የነገውን የብልፅግና ራዕይ የሚያመላክት የሀገራችን የከፍታ ዓርማ መሆኑን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩን አስመልከተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ እንኳን ለ19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሰላም አደረሰን በማለት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የመደመር መንግሥት ዋነኛ ትኩረት ኢትዮጵያን በአንድነት፣ በሰላም፣ በልማትና በሁለንተናዊ ብልጽግና ወደ ላቀ ከፍታ ማሸጋገር መሆኑን ያረጋገጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ሠንደቅ ዓላማችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ እንጂ የልዩነታችን ምንጭ መሆን እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህልና በእምነት የተለያየን ብንሆንም፣ በኢትዮጵያዊነታችንና በጋራ የልማት ራዕያችን አንድ መሆናችንን ያስረዱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመደመር ዕሳቤም ልዩነቶቻችንን እንደ ሀብት በመቁጠር፣ የጋራ ዕሴቶቻችንን በማጠናከርና በትብብር የሀገራችንን ታላቅነት በተግባር ለማረጋገጥ የሚያነሳሳን መሆኑን ገልጸዋል።

 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ታላቅ ብሔራዊ ቀን፣ ሠንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርገን እያውለበለብን ለአንድነታችን፣ ለሰላማችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለሀገራችን ብልጽግና ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር እንድናረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: