በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በየዓመቱ ለተጫዋቾች ዝውውር በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ሲደረግ ማየት የተለመደ ሆኗል። ክለቦች ውድ ዋጋ በማውጣት ስብስባቸውን ለማጠናከር ቢጥሩም፣ ከሜዳ ላይ ስልጠና ባሻገር ተጫዋቾችን በተሟላ መልኩ የሚያዘጋጅ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የአሠልጣኞች ቡድን መዋቅር በመገንባት በኩል ግን አሁንም ሰፊ ክፍተት ይስተዋላል።
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ በማሠልጠን ላይ የሚገኙት የሲዳማ ቡና አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ፣ የአዳማ ከተማ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በክለቦች የአሰልጣኞች ቡድን አወቃቀርና ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ ያላቸውን ምልከታ አጋርተዋል።
ያሬድ ገመቹ፡ “ውጤት የብዙ ባለሙያዎች የጋራ ድምር ነው”
የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እንደሚገልጹት፣ በዘመናዊ እግር ኳስ የአሠልጣኞች ቡድን አወቃቀር እጅግ ሰፊና ዘርፈ ብዙ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በክለቦች ውስጥ የሥነ ልቦና፣ የስነ ምግብ፣ የህክምና እና የቴክኒክ ክፍሎች ራሳቸውን ችለው እንደሚዋቀሩ ያነሳሉ። በኢትዮጵያ ግን ዋና አሠልጣኝ፣ ሁለት ረዳቶች፣ የበረኛ አሠልጣኝ እና አልፎ አልፎ የቴክኒክ ዳይሬክተር ከመያዝ የዘለለ ልምድ አለመኖሩን ይጠቁማሉ።
አሰልጣኝ ያሬድ በተለይ የስነ ልቦና ባለሙያ አስፈላጊነት ላይ ሲያብራሩ፣ ተጫዋቾች በማኅበራዊ ሚዲያ በሚደርስባቸው ጫና፣ በሽንፈት ወቅት እንዲሁም በግል ሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ቀውሶች ውስጥ ሲያልፉ ከስፖርት ሳይኮሎጂ ባለሙያዎች የሚያገኙት እገዛ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል።
በተመሳሳይ የተጫዋቾችን የሰውነት ግንባታና አቅም ለመጠበቅ የስነ ምግብ ባለሙያ መኖር መሰረታዊ መሆኑን ይጠቅሳሉ። እንደ አሠልጣኙ ገለጻ፣ ውጤት የሜዳ ላይ ስልጠና ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለሙያዎች ጥረት ድምር ውጤት ነው።
ፋሲል ተካልኝ፡ “ ተቋማዊ ሲስተም መዘርጋት የግድ ይላል”
የአዳማ ከተማው አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው፣ ቀደም ባሉ ዓመታት ዋና አሠልጣኙ የመጓጓዣ ትራንስፖርት ከማዘጋጀትና የምግብ ሁኔታን ከመቆጣጠር ጀምሮ ሁሉንም ሸክም ብቻውን ይሸከም እንደነበር ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት የረዳት አሠልጣኝ፣ የበረኛ አሠልጣኝ እና የአካል ብቃት አአሠልጣኞችን በመቅጠር ረገድ መሻሻሎች የታዩ ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
አሠልጣኝ ፋሲል በተለይ የቪዲዮ ትንተና በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ የሚፈጥረውን ለውጥ ያብራራሉ። ተጫዋቾች በቃል ከሚነገራቸው ይልቅ በቪዲዮ መረጃ ሲቀርብላቸው የሸፈኑትን ሜዳ፣ የታክቲክ አተገባበራቸውን እና ድክመቶቻቸውን በግልጽ ለመረዳት እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል። ይህም አሠልጣኙ ምክንያታዊ እርማት እንዲሰጥ እና የቡድኑም ሆነ የተጫዋቾቹ የግል አቅም እንዲያድግ ያደርጋል።
ክለቦች ለተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሱ ለአሠልጣኞች ቡድን ትኩረት አለመስጠታቸው መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት አሠልጣኝ ፋሲል፣ ክለቦች ተቋማዊ አሰራር ሊኖራቸው እና ተጠያቂነት ሊያሰፍኑ እንደሚገባ ያሳስባሉ። በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ እና የሊጉ አስተዳዳሪ አካላት የሚያወጧቸው ሕጎች ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙና በተግባር የሚፈጸሙ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በፀሎት ልዑልሰገድ፡ “ስራን አለመከፋፈል ለውድቀት ይዳርጋል”
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ፣ በአንድ ወቅት የተሳተፉበትን የሥልጠና ኮርስ በማስታወስ፣ አንድ አሠልጣኝ ሁሉንም ሙያ ደርቦ ሲሰራ የነበረበትን አሰራር አሠልጣኞች “ወንጀል የሰራንበት ወቅት ነበር” እስኪሉ ድረስ የተዛባ አሰራር እንደነበር ይገልጻሉ።
አሰልጣኝ በፀሎት በከፍተኛ ሊግ እያሠለጠኑ በነበረበት ወቅት ረዳት አሠልጣኝ ባለመኖሩና ፊዚዮቴራፒስት ጥሎ በመጥፋቱ ምክንያት ብቻቸውን ሁሉንም ስራዎች ለመሸፈን የተገደዱበትን ፈታኝ ወቅት አውስተዋል። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር በሜዳ ላይ የሚፈለገውን የታክቲክ እቅድ በአግባቡ እንዳይተገበር ማነቆ እንደሚሆንና እግር ኳስ የቡድን ስራ በመሆኑ ክፍተት መፈጠሩ እንደማይቀር ያረጋግጣሉ።
ክለቦች ለተጫዋች ከፍተኛ በጀት መድበው ያ ተጫዋች ሙሉ ብቃቱን እንዲያወጣ የሚያግዙትን የህክምና፣ የሪከቨሪ፣ የአካል ብቃት እና የቪዲዮ ባለሙያዎችን አለማሟላታቸው የግንዛቤ እጥረት መሆኑን አሠልጣኙ ያስረዳሉ። ለዚህም መፍትሔው በቅድሚያ በክለብ አመራሮች ዘንድ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የአሰራር ሥርዓትን በተመለከተ ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት እንደሆነ ያምናሉ።
የሦስቱም አሠልጣኞች ምልከታ የሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃውን የጠበቀ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን ከተፈለገ ሜዳ ላይ በሚታዩት ተጫዋቾች ዝውውር ላይ ብቻ ማተኮር እንደማይበጅ ነው። የክለብ አመራሮች እና የውድድሩ አስተዳዳሪዎች፣ ለተጫዋቾች ከሚወጣው ከፍተኛ በጀት ጎን ለጎን፣ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የአሰልጣኞች ቡድን መዋቅር መዘርጋት የውጤታማነት መሰረት መሆኑን ተገንዝበው በተግባር ሊሰሩበት ይገባል።
በእሱባለው ተሾመ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: