ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟ በተደጋጋሚ እንዲጠራ ባደረገው የአትሌቲክስ ስፖርት ውስጥ ከትናንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከዓለም ሀገራት በላይ ከፍ ብሎ ተውለብልቧል፡፡
ብሔራዊ መዝሙሯ ተደጋግሞ ተዘምሯል፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን የማሸነፊያ ምስጢራችን ነውና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጀግነውበታል፡፡ ተፎካካሪዎች በሰንደቅ ዓላማችን ውስጥ ባለው አሸናፊነት የመንፈስ ቅናት አድሮባቸዋል፡፡
66 ዓመታትን ወደኋላ! እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1960 ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ማራቶን ፈር ቀዳጅ አትሌት አበበ ቢቂላ ሮምን በባዶ ግሩ ሲወራት ለአሸናፊነቱ ምክንያት የሰንደቅ ዓላማው ክብር፣ የሀገሩ ጥልቅ መውደድ የባዶ እግር ህመሙን አስታግሶለት ነው፡፡
ከአበበ ቢቂላ መልስ በኦሊምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና አሸናፊዋ ሀገር ኢትዮጵያ በስፖርት ከፊት እንድትቀድም፣ ሰንደቅ ዓላማዋም ከፍ ብሎ እንዲውለብለብ በትውልድ ቅብብሎሽ ልጆቿ ድንቅ ጀብዱ ሰርተዋል፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ በኦሳካ መም ላይ ባጋጠማት ህመም መቀጠል የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ ተፎካካሪዎቿ ርቀዋት ቢሄዱም፣ የወከለችውን ህዝብና ሀገር አስቀደመችና ተፋለመች፡፡ ያኔ ጥሩነሽን ከቀቢጸ-ተስፋነት አስወጥቶ አሸናፊ ያደረገው የሰንደቅ ዓላማው ኃይል ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ የምንጊዜም ምርጡ የረጅም ርቀት ሯጭ ኃይሌ ገብረሰላሴ በሲድኒ እና አትላንታ ኦሊምፒክ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለብለብ አድርጓል። እስከ አሁንም ድረስ የሚታወሰው የቴርጋት እና የኃይሌ ገብረሰላሴን እልህ አስጨራሽ ፉክክር “ኃይሌ አሸናፊ መሆን የቻለው በአንበሳዊ ስነ ልቦና ነው” ሲል ኬንያው አትሌት ኢትዮጵያውያን ሀገርን ወክለው ከሮጡ እነርሱን ማሸነፍ ከባድ እንደሆነ መስክሯል፡፡
”ገና በለጋ ዕድሜዬ ለሀገሬ አንዳች ነገር የማድረግ ህልም ነበረኝ እና ያ ሆኖ በማየቴም እንባ ከውስጥ ፈንቅሎ ፈሰሰ“ ሲል ወቅቱን ያስታውሳል፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ለቁጥር አታካች የሆኑ ውድድሮችን ሩጦ አሸንፏል፤ ክብረ ወሰኖችንም ሰባብሯል፡፡ በአትሌቲክስ ያሉ የግል ክብሮችን ደግሞ ደጋግሞ ተጎናጽፏዋል፡፡ አንዳቸውም ግን በኦሊምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና ሀገሩን ካስጠራባቸው ውድድሮች ጋር እንደማይስተካከሉ ይናገራል፡፡
ልክ እንደ ኃይሌ ሁሉ ደራርቱ ቱሉ ከጉዳት እና ከህመም ጋር እየታገለች ሀገሯን አሸናፊ አድርጋለች። በባርሴሎና ምድር አንዲት ኢትዮጵያዊት አትሌት ከሰሀራ በታች ካለው የአፍሪካ ክፍል በኦሊምፒክ በሴቶች የመጀመሪያዋ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆና በመጠራት ሀገሯን አኩርታለች፡፡
ያሸንፋል ተብሎ የተገመተው ሲደክም ጭምር ሜዳ ላይ ስለሀገር ክብር አዳዲስ ጀግኖች መፈጠራቸው ህያው ምስክር ሆኖ የማሞ ወልዴ ታሪክ ይወሳል፡፡ ምሩጽ ይፍጠር በሞስኮ ኦሊምፒክ የሁለትዮሽ ባለ ድል ሆኖ ዓለምን ጉድ ያሰኘው ሃገሬን ከፊት አስቀድሜ ሌላው ከኋላ ይሰለፍ በሚል የአንበሳ ልብ ነው፡፡
ይህ የሰንደቅ ዓላማው ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማሸነፍ ልማዷነውና አትሌቶች እየተተካኩ ማሸነፍን ተለማምደዋል፡፡
ከአትሌት ቀነኒሳ በቀለ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ከመሰረት ደፋር እስከ አልማዝ አያና፣ ከገንዘቤ ዲባባ እስከ ለተሰንበት ግደይ፣ ከትዕግስት አሰፋ እስከ ታምራት ቶላ እንዲሁም ያሁኑ ዘመን አልጋውራሾች ጭምር ለባንዲራቸው ትልቅ የሚባለውን ውጤት አስመዝገብዋል፡፡
በኦሊምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና ብሎም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በተወከለችባቸው ውድድሮች ሁሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን ሯጮች በየዘመናቸው ሀገራቸውን አኩርተዋል፡፡ እርሷም ኮርታባቸዋለች፡፡
በእግር ኳሱ ዓለም የኢትዮጵያ የዘመናት ተሳትፎ ከፍታና ዝቅታ ወቅት ተጫዋቾች ለሀገራቸው ለፍተዋል። ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ግብጽን ስታሸነፍ በግል ብቃትና ባላቸው ልምድ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከተጋጣሚያቸው ያነሰ ታሪክ ያላቸው ቢሆንም ሀገርን አሸናፊ በማድረግ ወኔ ድልን አምጥተዋል።
ኢትዮጵያ ጨዋታ ሲኖራት በሰንደቅ ዓላማዋ ያጌጡ፣ ሰንደቅ ዓላማውን በስስት እያዩ ማሸነፍን ብቸኛ አማራጭ አድርገው ዜጎቿ ይዘጋጃሉ። ኢትዮጵያ ጨዋታ ሲኖራት ሁልግዜም ደጋፊዎች የኢትዮጵያን ስም እየጠሩ፣ ሰንደቅ ዓላማዋን እያውለበለቡ፣ ማንም ሊደፍራት የማይችል የአባቶቻቸው ምድር መሆኗን ያወሳሉ፡፡
ስፖርት በብዝሀነት ውስጥ ያለ፤ የሉዓላዊነት ምሰሶና የብዝሀነት መገለጫ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ ደግሞ በስፖርት ውስጥ ዋነኛው የማሸነፊያ ምክንያት ነው፡፡
ባንዲራ ኃይል፣ ጉልበት እና የማሸነፍ ምስጢር መሆኑን ስፖርተኞች ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያዊያን ውስጥ ሁሌም ህልው ሆኖ ይኖራል፡፡
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት ቀጥሎም ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስትመለስ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተገኙ ልጆቿ ናቸው ለዚያ ክብር ያበቋት፡፡
የአሸናፊነት ምልክት በሆነው ሰንደቅ ዓላማ በስፖርቱ ዓለም ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ያልተደረገውን፣ ያልተገመተውን አድርገውበታል፤ ሪኮርዶችን በጣጥሰውበታል፣ የማይታሰበውን ከውነውበታል፡፡ በዚህ ሰንደቅ ዓላማ ተጋጣሚና ተፎካካሪ ርዶበታል፡፡ ይህ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም ዘንድ የማሸነፍ አብነት ሆኖ አሁንም ቀጥሏል፡፡
በሀብታሙ ካሴ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: