Search

የኢትዮጵያ ብልጽግና በጠንካራ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ይገነባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ሰኞ ጥቅምት 02, 2019 112

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ እውነተኛ አጋርነት ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ በዛሬው ዕለት የሚድሮክ ዐውደ ርዕይ ሳምንትን አስጀምረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብልጽግና በጠንካራ የመንግሥትና የግሉ አጋርነት እንደሚገነባ ገልጸው፣ የግል ዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግርን በሚያሣልጡ ዘርፎች ላይ እንዲሠማራ ማበረታታትና መደገፍ አንዱ የመደመር መንግሥት ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም እንደ ሚድሮክ ያሉ ጠንካራ ሀገር በቀል ተቋማትን ማበረታታትና ዐቅማቸውን ማሳደግ ማለት የሀገርን ምርታማነት ማሳደግ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬና የግብር ገቢን ማሳደግ እንዲሁም የፈጠራና የቴክኖሎጂ ኀቅምን ማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል።

ሚድሮክ ከትናንት ስኬቶቹ ባሻገር፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ፣ በምርታማነትና በወጪ ምርት እንዲገነባ ጭምር እንደሆነ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የተቋሙ ልምድና ዘመናዊ አሠራሮች ለሌሎች ሀገር በቀል ተቋማት ሲተላለፉ፣ የአንዱ ስኬት የብዙዎች የዕድገት መሠረት እንደሚሆን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ብልጽግና በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን በግሉ ዘርፍና በማኅበረሰቡ ጥረት ጭምር የሚረጋገጥ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፤ በመንግሥት፣ በማኅበረሰቡና በግሉ ዘርፍ ጠንካራ አጋርነት፣ በጋራ ዐቅምና በጋራ ስኬት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እናረጋግጣለን ብለዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: