የኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ሲታወስ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የነጻነት፣ የሉዓላዊነት እና የኩራት ማኅደር ብቻ አይደለም።
የኢትዮጵያ ታሪክ ከፈተናዎች እና ከውድቀቶች ተነስተው በቁጭት የመለወጥ የጽናት ታሪክም ጭምርም ነው።
አብዛኞቹ በኢትዮጵያ የተከሰቱ የለውጥ ምዕራፎች የተጀመሩት በወቅታዊ ግፊቶች፣ በሥርዓታዊ ክፍተቶች እና በሕዝባዊ ቁጭት በተደገፉ ትግሎች ነበር።
ይሁን እንጂ የየዘመኑ ትልቁ የኢትዮጵያ ፈተና እና ድል የሚለካው ያንን ታሪካዊ ቁጭት ወደ ዘላቂ እና ተቋማዊ ሥርዓት በመቀየር ረገድ በሚመዘገበው ተጨባጭ ውጤት ላይ ነው።
ቁጭት ለአንድ ማኅበረሰብ የመነሻ ኃይል እንጂ ማድረሻ ሊሆን አይችልም። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ቁጭት መነሻ እንጂ ማድረሻም መዳረሻም አይሆንም፤ ማድረሻው ሥርዓት ሲሆን፣ መዳረሻው ደግሞ ሥልጣኔ ነው፤ ቁጭት ሥርዓትን እንዲወልድ ሰክኖ ማሰብን ይፈልጋል” ሲሉ የገለጹት ሀሳብ የዚህን ሽግግር መሠረታዊ ፍልስፍና ያመላክታል።
የመደመር መንግሥት በቁጭት የመጣውን የለውጥ ፍላጎት ወደ ሰከነ አስተሳሰብ እና ተጨባጭ ቅርጽ ለመቀየር በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል።
በታሪካዊ የለውጥ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያን ከገጠሟት ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች በመማር ወደ ጠንካራ ተቋማት ግንባታ የመሸጋገር ጉዞው በተሳካ ሁኔታ ቀጥሏል።
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የሀገረ-መንግሥት መዋቅር ለማጽናት፣ የዲጂታል እና የኢኮኖሚ መሠረቶችን በዘላቂነት ለመዘርጋት በርካታ ቁልፍ ተቋማት ተገንብተዋል።
ከእነዚህም መካከል አዲስ መዋቅር ይዘው ሀገራዊ የካፒታል አቅምን እያሳደጉ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ማዕከል የሆነው የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ሥርዓት፣ እንዲሁም የቴሌኮም ዘርፉን በማዘመን እና የቴሌብር አገልግሎትን በማስፋፋት የፋይናንስ አካታችነትን ያረጋገጠው ኢትዮ ቴሌኮም ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህ ጎን ለጎን የሁሉንም ዘርፎች ዕድገት የሚደግፈው ሁሉን አቀፍ የማክሮ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ማጠናቀቂያ ምዕራፍ የዚሁ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ ጥንካሬ ግልጽ ማሳያዎች ናቸው።
እነዚህ እርምጃዎች ኢትዮጵያ ከጊዜያዊ የችግር ምላሽ ወጥታ ወደ ዘላቂ የልማትና የመዋቅር ግንባታ መሸጋገሯን ያረጋግጣሉ።
ታሪክ እንደሚያስተምረን ቁጭት የአንድን ማኅበረሰብ ስሜት ቀስቅሶ አቅጣጫ ሊያስይዝ ይችላል፤ ነገር ግን ዘላቂ ሽግግር ማምጣት የሚችለው ያ ቁጭት መሠረት ያለው አሠራር፣ ሕግ እና ጠንካራ ተቋማዊ ሥርዓት ሲበጅለት ብቻ ነው።
የለውጥ ጉዞው ከግለሰባዊ ወይም ከጊዜያዊ ፍላጎቶች ወጥቶ ወደ ተቋማዊ አስተዳደር መሸጋገሩ እውን የሆነ ታሪካዊ ሂደት ነው።
ከስሜታዊ ምላሽ ይልቅ፣ ዛሬ ላይ የሚደረጉ የፖሊሲ ውሳኔዎች እና ተቋማዊ መዋቅሮች ሕግን፣ ብቃትን እና ሀገራዊ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ እርምጃዎች ሀገርን በጽኑ መሰረት ላይ የሚያቆሙ ናቸው።
እስከ 2050 ባለው ጊዜ ውስጥ የተያዘውን ትልቅ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የብልጽግና ራዕይ እውን ለማድረግ ይህ ከቁጭት ተነስቶ በሥርዓት የማለፍ እና ወደ ሥልጣኔ የመድረስ ታሪካዊ ሐዲድ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ዛሬ የሚገነቡት እና የሚተከሉት ጠንካራ ተቋማት ነገ የሚመጣውን ትውልድ ከብዙ ውጣ ውረዶች የሚታደጉ መሠረቶች ናቸው።
በመደመር መንግሥት የሚመራው የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ከትናንትናው ቁጭት ተምሮ ዛሬን በጠንካራ ሥርዓት እየገነባ፣ ለነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: