በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መርሆዎች እና በመንግሥታት መካከል በሚኖር ሕጋዊ ግንኙነት ውስጥ የሉዓላዊነት መከባበር፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና የሰከነ ውይይት ቀዳሚ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው።
የግብፅ ከፍተኛ አመራሮች ከዲፕሎማሲያዊ ወግ እና ደንብ አኳያ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የጣሱ መግለጫዎችን በየመድረኩ ማሰማታቸውን ገፍተውበታል።
“በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ፕሮጀክት እንዲሠራ አንፈቅድም፣ ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛ ላይ አሉ” እንዲሁም “ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር እና የሕንድ ውቅያኖስ ተጋሪ እንድትሆን አንፈቅድም” የሚሉት የባለሥልጣናቱ መግለጫዎች ከዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ውጪ የሆኑ ንግግሮች ናቸው።
ግብፅ ይህንን መሰል ቋንቋ የምትከተለው በዓባይ ተፋሰስ ላይ ለዘመናት ስትከተለው የነበረው ብቸኛ የበላይነት እና ፍትሐዊ ያልሆነ ስምምነት በኢትዮጵያ የልማት ቁርጠኝነት ምክንያት ሙሉ በሙሉ በመፈራረሱ ነው።
በገዛ መሬቷ ላይ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት በፍትሐዊነት ከመጠቀም ኢትዮጵያን ማገድ ያቃታት ካይሮ፤ አሁን ላይ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም ለመንሳት እና አካባቢውን ለማቀበል ጎረቤት አካላትን እንደ ማስፈጸሚያ ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት አፋጥናለች።
የሦስትዮሽ እና አራትዮሽ ስብስቦች፣ የጦር መሣሪያ ዝውውር እና የሠራዊት ስምሪት እንቅስቃሴዎች ጊዜ ያለፈበት የኢትዮጵያን የመክበብ ስትራቴጂ ዳግም ለመሞከር የሚደረጉ ከንቱ ጥረቶች መሆናቸው ተመላክቷል።
የግብፅ መሪዎች ከኢትዮጵያ በላይ ለጎረቤቶቿ ተቆርቋሪ ለመምሰል እና ለሕዝቦቻቸው ሉዓላዊነት እንቆማለን በማለት በየመድረኩ ቢደሰኩሩም፤ ታሪክ እና ተጨባጭ እውነታዎች ግን ፍጹም የተለየ እውነትን ይመሰክራሉ።
እነዚህ ሀገራት አስቸጋሪ ጊዜያት እና የታሪክ አጋጣሚዎች ውስጥ ሲወድቁ ለሰላማቸው የልጆቿን የደም መስዋዕትነት ጭምር የምትከፍለው ኢትዮጵያ ናት።
ሶማሊያ በአሸባሪዎች ስትታመስ ኢትዮጵያ የደም ዋጋ ከፍላ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲኖራት ያደረገች ሲሆን፣ ዛሬም ቢሆን ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት ትልቅ መስዋዕትነት እየከፈለች ትገኛለች።
በሌላ በኩል ግብፅ ለነዚህ ወገኖች ያላት ፍላጎት ሰላማቸው እንዲጠበቅ እና ልማታቸው እንዲረጋገጥ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ማበሳጫ እና የጂኦፖለቲካ ጫና ማሳደሪያ አድርጎ የመጠቀም እኩይ ዓላማ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ያላት እውነተኛ ፍላጎት ማሳያ ከኬንያ፣ ጂቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ያሏት ዘመናዊ የልማት ትስስሮች ናቸው።
ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር የገነባችው የላፕሴት የልማት ኮሪደር፣ የድንበር ላይ ነፃ ንግድ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር እንደሚያሳየው ፍላጎቷ የጋራ ዕድገትን፣ የኢኮኖሚ ውህደትን እና የሰከነ ጎረቤትን ነው።
ይህ አቀራረብ ከኃይል አሰላለፍ ይልቅ የሕዝቦችን ትስስር እና የጋራ ብልፅግና የሚያስቀድም ሲሆን፤ ለግብፅ ግን ይህን ዓይነቱ በጋራ የማደግ አካሄድ እንቅልፍ የሚያሳጣት ሆኗል፡፡
የሆነ ሆኖ በይፋ በሕግ የጸናው የዓባይ ተፋሰስ የቋሚ ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) እና ሥራ የጀመረው የዓባይ ተፋሰስ ኮሚሽን የካይሮን የታሪካዊ ስምምነቶች ሞግዚትነት ሙሉ በሙሉ አክስመውታል። የተፋሰሱ ሕዝቦች እና መንግሥታት በጋራ እና በፍትሐዊነት የመጠቀም መብታቸውን በሕግ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር እና የወደብ አማራጭ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የቀጣናውን የጋራ ዕድገት ታሳቢ ያደረገ እንጂ የማንንም ሉዓላዊነት የሚጋፋ አይደለም።
የግብፅ መሪዎች ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያን ዕድገት የማደናቀፍ ከንቱ ሩጫ ዛሬም እንደ ትላንቱ ፍሬ አልባ ሆኖ ይቀራል።
የግብፅ የቃላት ፉከራም ሆነ በቀጣናው ላይ የምታደራው የሴራ ድር፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት እና የብልፅግና ጉዞ የሚያስቆምበት ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል የለውም።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: