የኢትዮጵያ ሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሰው ኃይል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ስኬት ቁልፍ እና አስተማማኝ መሠረት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሜቴዎሮሎጂ መሰል መሠረታዊ ተቋማት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ተቋማዊ አቅማቸው ካልጎለበተ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የ1987ቱን ድርቅ እንዲሁም የቅርብ ጊዜያት የክረምት እና የበጋ ወቅቶች ትንበያዎችን በማንሳት ተቋሙ ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃዎችን በጊዜ በመስጠቱ መንግሥት ቀድሞ እንዲዘጋጅ እና የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው "የተቋሙ መረጃዎች የየትኛውን አካባቢ እርሻ ማዘግየት ወይም ማፋጠን እንዳለብን፣ ምን ዓይነት ዘር መጠቀም እንደሚገባ እና ማዳበሪያን የት ቦታ መጠቀም እንዳለብን ቀድመን ለማቀድ ሰፊ ዕድል ፈጥረዋል" ብለዋል።
የሜቴዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አገልግሎት በግብርናው ዘርፍ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ከጤና፣ ከውኃ ሀብት ልማት፣ ከንፋስና ከውኃ ኢነርጂ ማመንጨት፣ ከምግብ ዋስትና፣ ከአደጋ ስጋት ሥራዎች እና ከአቪዬሽን ደኅንነት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል።
የትኛውንም ዘርፍ በውጤታማነት ለመመራት አስተማማኝ ዳታ እና መረጃ ማግኘት ግድ እንደሚልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ለአብነትም ባለፉት 8 ዓመታት የተከናወኑት የአረንጓዴ ዐሻራ እና የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሮች ከሜቴዎሮሎጂ መረጃ ጋር ተቀናጅተው ሲሠሩ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ችግኞች የንፋስ ግፊትን የሚከላከሉበትን፣ ዝናብ የሚስቡበትን እና የጎርፍ አደጋዎችን የሚቀንሱበትን ሂደት በጥናት እና በዳታ በመደገፍ ረገድ የተቋሙ ሚና እጅግ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
"አሁን ላይ ተቋሙ ከሳተላይት መረጃዎች በተጨማሪ በየወረዳው ካስቀመጣቸው የዳታ ማዕከላት መሣሪያዎች መረጃዎችን እየሰበሰበ እና በጥልቀት እየተነተነ ለተጠቃሚዎች መስጠት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ደረጃ ልክ ጥራት እንዳለው መሠረተ ልማት ሁሉ ለኢኮኖሚ፣ ለኤክስፖርትና ኢምፖርት ንግድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ከፍ ያለ እና የሚያኮራ የሜቴዎሮሎጂ አቅም ባለቤት መሆኗን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደፊት የራሷ ሳተላይት ኖሯት መረጃዎችን በቀጥታ ከሳተላይቱ የምታስተሳስርበትን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
መረጃን በመጠቀም መብላት፣ ኢነርጂ ማመንጨት እና ከአደጋዎች ራስን መጠበቅ ለቀጣይ የስትራቴጂያዊ መሻቶች ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ተቋሙ አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ ረጅም ዓመታትን የፈጀ በመሆኑ፤ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ወጣቶች ተቋሙን እየመጡ እንዲጎበኙና እንዲማሩ ጥሪ ቀርቧል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: