Search

ምክር ቤቱ ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የብድር ስምምነትን አፀደቀ

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 52

7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባው በኢፌዴሪ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ145.8 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የብድሩ ዓላማ የአዲስ አበባን የኃይል ማስተላለፊያ መረብ ለማጠናከር፣ አዳዲስ የኃይል ጣቢያዎችን መገንባትና ነባሮቹን ማሻሻል እንዲሁም የመሬት ውስጥ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም፤ ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) አስተማማኝና ዘመናዊ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የብድር ስምምነቱ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ብድሩ ቀላልና አነስተኛ የገንዘብ ጫና የሚፈጥር ተብሎ የተገለጸ ሲሆን የ6 ዓመት የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ በ 31 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተብራርቷል።

ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለኃይል ዘርፍ ማሻሻያ፣ ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተፈረመውን የ145.8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ ቀላል የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅን፤ አዋጅ ቁጥር 1441/2019 አድርጎ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: