Search

የተሰበረው የድህነት ትርክት እና ያበበው የኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 29

ለአስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ቱሪዝም በሁለት መሠረታዊ የታሪክ እና የአስተሳሰብ ሰንሰለቶች ተተብትቦ ቆይቷል፡፡

በአንድ በኩል ቅርሶችን እና ታሪካዊ እሴቶችን የጋራ ማንነት መገለጫ ከማድረግ ይልቅ እንደ ፖለቲካዊ ዕዳና የመጠላለፍ መድረክ የመመልከት አባዜ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘርፉን እንደ ኢኮኖሚ ምሰሶ ሳይሆን እንደ ተቀጽላ የገቢ ምንጭ የቆጠረ አነስተኛ ምልከታ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደገለጹት ይህ ዘመን ያለፈበት እሳቤ ተሰብሮ ቱሪዝም ወደ ብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ የገጽታ ግንባታ እና የማክሮ-ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተርነት የተሸጋገረበት አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል።

ይህ አዲስ ምዕራፍ በቅድሚያ የሚጀምረው ከትርክት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ቅርሶች እና ታሪካዊ ክስተቶች የአንድነት ማሰሪያ ከመሆን ይልቅ "የአንተን ቅርስ አግዝፈህ፣ የእኔን ታሳንሳለህ" በሚል የጎራ ፉክክር ሲታዩ ቆይተዋል።

የመደመር መንግሥት ይህንን የተዛባ አመለካከት በመሠረታዊነት በመቀየር በሰሜን ከላሊበላ ድንቅ የውቅር አብያተ-ክርስቲያናትና ከፋሲል ግቢ እስከ ደቡብ ምሥራቁ የሶፍ ዑመር ዋሻ እና የዛሬ 800 ዓመት ጥንታዊ የመስጂድ ሥልጣኔ ድረስ ያሉት ሀብቶች የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ በረከቶች ሆነው እንዲታዩ አድርጓል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት የጸሐይ አውሮፕላንን እና ጥንታውያን ንዋየ-ቅድሳትን ጨምሮ 40 የሚሆኑ በልዩ ልዩ ዘመናት ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱትም ይኸው የጋራ ክብር የማጽናት አካል በመሆኑ ነው።

ይኸው እሳቤ በውጭው መድረክ ለዘመናት ቅኝ ካለመገዛት ታሪካዊ ኩራት ጋር በተያያዘ በውጭ ኃይሎች የተለጠፈብንን "የረሃብ እና የድርቅ መገለጫ" ስም በገሃድ በሚታዩ የመዳረሻ ልማቶች በተግባር የመቀየር ስትራቴጂ ነው።

ይህ የትርክት ሽግግር ከኢኮኖሚው አወቃቀር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ግብርና ላይ ብቻ ጥገኛ በሆነ አካሄድ ያሳለፈችውን አመለካከት ለመስበር፣ አዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪን፣ ማዕድንን፣ ቴክኖሎጂን እና ቱሪዝምን በአምስት ምሰሶነት አሰናስሏል።

ዓለም አቀፉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በየዓመቱ 12.6 ትሪሊየን ዶላር እና ከ370 ሚሊየን በላይ የሥራ ዕድል የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ገበያ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ሀብት ተገቢውን ድርሻ እንድትወስድ ዘርፉ የሌሎች ክፍለ-ኢኮኖሚዎች የገበያ ድልድይ ሆኖ ተዋቅሯል።

ቱሪዝም ጎብኚው መጥቶ አይቶ ብቻ የሚሄድበት ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳስቀመጡት "ልቡ ተደስቶ፣ ኪሱ ተራቁቶ የሚመለስበት" እውነተኛ የንግድ ልውውጥ እንዲሆን ተደርጓል።

የቱሪዝም እምቅ አቅም ያለ መሠረተ ልማት ትርጉም አልባ በመሆኑ፣ መንግሥት ዘርፉን በአራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ከፍሎ ሰፊ ግንባታ አካሂዷል።

የመስህብ ስፍራዎችን በላቀ ደረጃ ማልማት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሪዞርቶች እና የማረፊያ ሥፍራዎችን ማዘጋጀት፣ ከአዳዲስ መዳረሻዎች ጋር የተሳሰሩ መንገዶች እና አዳዲስ አየር ማረፊያዎችን መገንባት እንዲሁም መረጃን እና የጉዞ ቦታዎችን በቅድሚያ በበይነ-መረብ ለማስያዝ የሚያስችል የዲጂታል ሥነ-ምህዳር መዘርጋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

እነዚህን ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ የተከተለው የፋይናንስ አካሄድ ደግሞ የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሕዝብ ቅንጅት ነው፡፡

በገበታ ለሸገር፣ ለሀገር እና ለትውልድ ፕሮጀክቶች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በቀጥታ ሀብት በማዋጣት እና ተከታይ ኢንቨስትመንቶችን በመክፈት አጋር ሲሆኑ ማኅበረሰቡም አካባቢን በመንከባከብ የጥቅሙ ቀጥተኛ ተካፋይ ሆኗል።

በተጨማሪም ከፈረንሳይ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ከጣሊያን እና ከቻይና መንግሥታት ጋር የተደረጉ ስትራቴጂካዊ የሀብትና የዕውቀት ትብብሮች የዘርፉን አቅም አጎልብተውታል።

ይህ የተቀናጀ ጥረት ያስገኛቸው ውጤቶችም በተጨባጭ ቁጥሮች ተረጋግጠዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከ1.4 ሚሊየን በላይ የውጭ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን ከዘርፉ ከ5.2 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል።

ይበልጥ የሚያስደንቀው ደግሞ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ያሳየው መነቃቃት ነው፡፡ ከ50.16 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎች ጉብኝት በማድረጋቸው ከ79 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

በተመሳሳይ መልኩ በጉባኤ፣ በማበረታቻ ጉዞ፣ በስብሰባ እና በዐውደ-ርዕይ ቱሪዝም ዘርፍ 204 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ከ166 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ተስተናግደዋል።

ሆኖም የቱሪዝም መሠረተ ልማት እና የመንግሥት ፖሊሲ ብቻቸውን ዘላቂ ውጤት ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ዘርፉ የሚጠይቀው ትልቁ ጥረት የባሕሪ እና የአስተሳሰብ ለውጥ ነው።

ከአውሮፕላን ማረፊያ ተሳፋሪን የሚቀበል የታክሲ አሽከርካሪ መልካም ገጽታን ከመገንባት፣ ሆቴሎች ንጽህናን እና ደረጃውን የጠበቀ እንክብካቤ ከማረጋገጥ እንዲሁም የሚዲያና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ክብር እና እምቅ አቅም ገልጦ ከማሳየት አንጻር የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የቱሪዝም ልማት የተለመደውን የቢሮክራሲ አሠራር ጥሶ ያለፈ፣ የትርክት ለውጥ ያመጣ፣ የዜጎችን አንድነት ያጠናከረና ኢኮኖሚውን በብዙኃ-ዘርፍ ያስተሳሰረ የለውጥ እንቅስቃሴ ነው።

በመሆኑም ይህንን ዕድል አሟጥጦ በመጠቀም ኢትዮጵያን በልኳ ማሳየት እና የሀብቷ ተጠቃሚ መሆን የሁሉንም ዜጎች ቀጣይነት ያለው ርብርብ የሚጠይቅ ብሔራዊ አደራ ነው።

#የመደመርመንግሥት

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: