Search

ቀድመው አስበው ለሚጠብቁ ብርቱዎች ምንዳው ብዙ ነው፤ ተለዋዋጩ የዓለም ምህዳር እና የኢትዮጵያ የማይቀለበስ የባሕር በር ሉዓላዊነት

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 46

ዛሬ ዘመኑ ፈጣን፣ ያልተጠበቀና እጅግ ተለዋዋጭ በሆኑ ሁኔታዎች የሚታዩበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ምህዳሮች ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተቀየሩ ይገኛሉ።

ነባር የኃይል አሰላለፎች እየፈረሱ፣ አዳዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጎራዎች በሚፈጠሩበት በዚህ ዘመን፣ ነገሮች ወዴት እንደሚጓዙ በእርግጠኝነት መተንበይ አዳጋች ሆኗል።

ታሪክ ወደየትኛው አዲስ ምዕራፍ እንደሚያደርሰን በግልጽ በማይታወቅበት በዚህ መንታ መንገድ ላይ መሆናችን ደግሞ ቀድሞ መዘጋጀትና ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይላል።

በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም የባሕር በሮችና የባሕር ላይ የንግድ መስመሮች የጂኦፖለቲካ ፍልሚያ እና የኃይል ሚዛን ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል።

ዛሬ ላይ የዓለም አቀፍ ንግድ፣ የምግብና የእቃ አቅርቦት ሰንሰለት እንዲሁም የኃይል አቅርቦት ዋነኛ የደም ሥር የሆኑት የባሕር በሮች ናቸው።

ዓለም አቀፋዊ ውጥረቶችና ግጭቶች በሚበዙበት ወቅት ደግሞ የቀጥተኛ ባሕር በር ባለቤት ያልሆኑ ሀገራት ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂየዊ ደኅንነት ሥጋቶች ይጋለጣሉ።

ይህም የሚያሳየን ትልቁ እውነታ፣ የባሕር በር በቀላሉ የወደብ አገልግሎት የመግዛት ጉዳይ ሳይሆን የሀገራትን ደህንነት፣ የንግድ ዋስትና እና ቀጣናዊ ተፅዕኖ የመወሰን አቅም ያለው መሠረታዊ መዋቅር መሆኑን ነው።

በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ እንደተገለጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "መጪውን ዘመን ቀድመው አስበው የሚያመጣውን አዲስ ነገር ከወዲሁ ገምተው፣ በተጠንቀቅ ለሚጠብቁ ብርቱዎች ምንዳው ብዙ ነው" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ ጥልቅ ንግግር ለነገው ተለዋዋጭና ብዙ ለውጦችን ለሚያስተናግደው ዓለም ዛሬ ላይ ተጠንቅቆና ቀድሞ መዘጋጀት የድል አድራጊነትና የህልውና ቁልፍ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

በማይታወቅ እና ስፍር ቁጥር በሌላቸው ውጣ ውረዶች በተሞላው ዓለም ውስጥ ነገን መረዳት እና ለሚመጡት ማዕበሎች ቅድመ ዝግጁ ማድረግ የህልውና ጉዳይ ነው።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና በቀጣናው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ ሀገር፣ የወደፊት እጣ ፋንታዋንና የንግድ ደህንነቷን በሌሎች መልካም ፈቃድና ጊዜያዊ ሁኔታዎች ላይ ብቻ ጥላ መጓዝ አትችልም።

ለዚህም ነው ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመሄድ በአለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት የጀመረው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት የሚነሳው ሃሳብ የፍትህ፣ የንግድ ዋስትና እና የቀጣናዊ መረጋጋት ቁልፍ እንደሆነ በሰፊው እየታመነበት መጥቷል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በቅድመ-ዝግጁነት መርህ ቀድማ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ፍጹም ተገቢ፣ ወቅታዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነትን ያገኘ ብሔራዊ አጀንዳ ነው።

ይህ አካሄድ የሌሎችን ጥቅም የሚጎዳ ሳይሆን፣ በፍትሃዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ፣ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚያፋጥንና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ አርቆ አሳቢ አካሄድ ነው።

ስለሆነም፣ ይህ ትውልድ የዘመኑን ፈጣን ለውጥና የጂኦፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ቀድሞ በመረዳት፣ ሀገራችን ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቷ የሆነውን የባሕር በር ባለቤትነት እንድታረጋግጥ የተጀመረውን ጥረት በጋራና በቁርጠኝነት ሊደግፈው ይገባል።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: