Search

የመደመር እሳቤ እና የኢትዮጵያ አዲሱ የልማትና የስልጣኔ ምዕራፍ

ማክሰኞ ጥቅምት 03, 2019 53

ኢትዮጵያ ለዘመናት የገጠሟትን ውስብስብ ምጣኔ ሀብታዊ ተግዳሮቶች ተሻግራ እንድትዘልቅ ያደረጋት ታላቅ ኃይል የሀገር በቀል እውቀቶችና የአብሮነት ጥምረት ውጤት ነው።

ጥንታዊው የስልጣኔ ታሪካችን በጋራ የመኖር፣ የመደጋገፍ እና ልዩነቶችን አቻችሎ የመጓዝ ጥበብ ላይ የተመሠረተ እንደነበረው ሁሉ፣ የዛሬው ኢኮኖሚያዊ ሕዳሴያችንም በተጨባጭ ሀገራዊ አቅምና በመደመር እሳቤ ላይ ቆሞ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ የታየው ትልቅ መዋቅራዊ ሽግግር ትናንት ይስተዋል የነበረውን ጥገኝነት በመስበር ያለንን ተደማሪ ሀገራዊ አቅም በተግባር ማረጋገጥ ችሏል።

በቀደሙት ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና በተፈጥሮ ዝናብ ላይ ብቻ የተመሠረተ ስለነበር፣ ይህ ክፍተት ሀገራችን የውጭ እህል እርዳታና ድጋፍ እንድትጠባበቅ አድርጓት ቆይቷል።

ሆኖም ይህ ታሪካዊ ስብራት በመደመር እሳቤ በተቀረፁ ሀገር በቀል ስትራቴጂዎች ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍጆታዋን ከመሸፈን አልፋ  ለሌሎች መትረፍ የምትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች።

በተጨማሪም በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው የሩዝ ልማት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዟችንን አስተማማኝ አድርጎታል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በየጓሮው የተጀመረው አጠቃላይ የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የወተትና የማር ምርት ዕድገት የዜጎችን የአመጋገብ ሥርዓት ከማሻሻል በተጨማሪ የከተማና የገጠር አባወራዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳደገ ነው።

በአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው የኢኮኖሚውን መሠረት ከማጠናከር በተጓዳኝ ለአፈር መሸርሸር፣ ለድርቅና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ከባቢን ፈጥሯል።

ከዚህ ቀደም በውስን ምርቶች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የቆየው ሀገራዊ ኢኮኖሚ አሁን በባለ ብዝኃ ዘርፍ ምጣኔ ሀብት እየተተካ ነው።

የመደመር ስልጣኔ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ፣ ታላቅነት በምኞት ሳይሆን በጋራ አቅም፣ በፈጠራና በተግባር የሚገኝ መሆኑን ማረጋገጡ ነው።

በተደመረ አቅም ያገኘናቸውን ተጨባጭ የልማት ውጤቶች አጠናክረን በማስቀጠል ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ገናና ሀገር ማድረግ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው።

በሃና ምንዳሁን

#የመደመርመንግሥት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: