Search

ዲጂታል ኢትዮጵያ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ከፍታ

ረቡዕ ጥቅምት 04, 2019 88

የሰውሰራሽ አስተዉሎትና የዲጂታል አብዮት የፈጠራ አቅም ለሀገራዊ ብልፅግና ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ታሪካዊ ሽግግር እያደረገች በምትገኝበት በዚህ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሀገራችንን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ዋና ዋና የልማት ሞተሮች ሆነው ወጥተዋል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመቀበል ማህበረሰባዊ ፈተና የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ግን ማህበረሰቡ ጠቀሜታውን ተገንዝቦ ሕይወቱን ለማቅለልና ጊዜ እና ጉልበትን ለመቆጠብ እየተጠቀመበት ይገኛል።

መንግሥት የቴክኖሎጂ ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ በመቅረፅ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ማቋቋሙ ለትውልድ የሚሻገር ሀገራዊ ዐሻራ ሲሆን፣ በጤና፣ በግብርና እና በትምህርት ዘርፎች ግዙፍ አስተዋፅኦ በማበረከት ሀገር በቀል ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት የሚያስችል የክህሎት መሰረት ጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የሰው ሰራሽ አስተውሎት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፣ አፍሪካ የፈጠራው መሪና ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግም በምርምርና ክህሎት ላይ ያተኮሩ ኢንቨስትመንቶችን በማጠናከር ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር ጥረት እያደረገች ነው።

በከተሞች ከተተገበረው ዘመናዊ የኮሪደር ልማት፣ በግብርናው እመርታ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በፋይናንስ ዘርፍ መከፈት ባሻገር የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሚወስነው ዋናው ምሰሶ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ነው።

በእውቀትና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ የመገንባት ጉዞዋን ያፋጠነችው ሀገራችን፣ በመንግሥት አገልግሎቶች ግልፅነትና እንደ ፋይዳ፣ መሶብ እና ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያዎች ባሉ አሰራሮች ከአካታች ዲጂታል ሥርዓት ጋር ተያይዛለች።ከ130 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው ህዝብ አብዛኛው ወጣት በመሆኑ ይህንን ሀብት በቴክኖሎጂ ማነፅ የዲጂታል አብዮቱ ቁልፍ ነው።

ወጣቱ ችግር ፈቺና የራሱን ሥራ የሚፈጥር እንዲሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስታርት አፖችን በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ሚና እያከናወነ ይገኛል። በተለይም ታሪካዊው ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ወጣቶች በሶፍትዌር ልማት፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአንድሮይድ እና በኤአይ በነፃ ሰልጥነው የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ትልቅ የክህሎት ድልድይ ሆኗል።

በአጠቃላይ የመንግሥት ፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት እና የወጣቱ የፈጠራ አቅም ተቀናጅተው የሚተገበሩበት ይህ ሂደት በ2030 ኢትዮጵያን በዲጂታል ኢኮኖሚ የጎለበተች ሀገር የማድረግ ህልምን በፅኑ መሰረት ላይ ጥሎታል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: