የአንድ ሀገር እውነተኛ ነፃነት የሚለካው በድንበሯ መከበር ብቻ ሳይሆን ራሷን የምታስብበትንና መጻኢ ዕድሏን የምትቀርጽበትን የአስተሳሰብ ሉዓላዊነት በማረጋገጧ ጭምር ነው።ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ የውጭ ወረራዎችን በጀግንነት መክታ ብትቆይም፣ የፖለቲካ ልሂቃኗ ከባሕር ማዶ በተዋሷቸው ያልተገሩ ርዕዮተ ዓለሞች ሀገራችንን የሙከራ ጣቢያ አድርገዋት ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ ለሌሎች እሳቤ ሲባል ኢትዮጵያን ከመቀየር ይልቅ፣ ለኢትዮጵያ ሲባል የሌሎችን እሳቤ አቃንቶ መቀበል የዘመናችን ትልቁ የፖለቲካ እና የሥልጣኔ እጥፋት ነው።
ይህ ምልከታ ኢትዮጵያን ከውሰት አስተሳሰቦች ጥገኝነት አውጥቶ፣ በራሷ ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ ሥነ-መንግሥት እንድትገነባ የሚያስችል መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው።
የዓለም የሥልጣኔ ታሪክም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሐቅ ነው። የአውሮፓ ሥልጣኔ የቆመው በአውሮፓዊ ባህል መሠረት ላይ ሆኖ፣ በግሪክ ፍልስፍና ተቃኝቶ እና በሮማውያን የሥነ-መንግሥት ዘይቤ ተገንብቶ ነው።
በተመሳሳይ የምሥራቅ እስያ ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ ተአምር የፈጠሩት፣ ከእስያዊ ባህል ጋር በተስማማው የኮንፊሺየስ እሳቤ ላይ ተመሥርተው፣ ዋናውን ጥንስስ ራሳቸው ጠንስሰውና የሌሎችን ግብዓት ከሚፈልጉት ጣዕም ጋር መስማማቱን አረጋግጠው በመውሰዳቸው እንጂ ማንነታቸውን በመደምሰስ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም ፈተናዎች ያልበገሯት፣ ችግሮች ያልበጠሷት፣ ርዕዮተ ዓለሞች ያልቀየሯትና የፖለቲካ ልሂቃን ያልከፋፈሏት ጠንካራ ሀገር ናት። ይህ ጽናት የተገኘው ሕዝቧ ብዝኃነትን ከአንድነት፣ የእምነት ልዩነትን ከእሴት ትስስር፣ አካባቢያዊነትን ከሀገር፣ የግል ፍላጎትን ከቡድን እንዲሁም ትናንትን ከዛሬ እና አቅምን ከአቋም ደምሮ ስለሚጓዝ ነው።
ስለዚህ መደመር በትውልድ ቅብብሎሽ የዳበረውን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ወረት ፈልፍሎ፣ ከባሕር ማዶ ጥበቦች ጋር በማጣጣም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ የማድረግ ፍኖት ነው።
ይህ ሀገር በቀል የሥልጣኔ እሳቤ ከንድፈ-ሐሳብ አልፎ በተግባር የሚገለጸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከድህነት አረንቋ በማውጣትና ፈጣን ልማትን በማረጋገጥ ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያ የምትመራበት የመደመር እሳቤ የሀገራችንን ሙሉ ትኩረት ወደ ልማት ከፍታ እንዲያመለክት አድርጎታል።ባለፉት ዓመታት ስንሞክር፣ ስናርምና የሌሎችን ተሞክሮ ከራሳችን ጋር ስናስማማ በቆየንበት ሂደት በብዙ መስኮች ተጨባጭ ፍሬዎች ተገኝተዋል። በግብርናው መስክ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተደረገው ሽግግር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፈውና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ ዐሻራ እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬቶች የዚሁ ማሳያዎች ናቸው።
በተጨማሪም በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ የተገነቡ ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ንቅናቄዎችና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተመዘገበው የፋይናንስ አብዮት፣ ኢትዮጵያ ኃይሏን፣ ጊዜዋንና ሀብቷን ዜጎቿን ለመለወጥ እያዋለች መሆኗን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በሙሉ አቅሟ ወደ ብልጽግና እና ከፍታ እየገሰገሰች ትገኛለች። ያለንን ነባር የሥልጣኔ ወረት ይዛ፣ በጎደለው ደግሞ ከዓለም ጥበቦች እየሞላች የምትጓዘው ኢትዮጵያ፣ የራሷን የብልጽግና ታሪክ በራሷ ማሰቢያ ቋንቋ የምትጽፍበትን ጠንካራ ምዕራፍ ከፍታለች።
#ትልቅ_ሕዝብ፣ #ትልቅ_ሀገር እና #ታላቅ_ርዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያ፣ ከውሰት አስተሳሰብ ጥገኝነት ተላቅቃ በራሷ የሥልጣኔ ሉዓላዊነት ወደ ታሪካዊ ከፍታዋ የምታደርገውን ግስጋሴ በድል ታጠናቅቃለች፡፡
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: