ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ የሉዓላዊነት እና የነፃነት ተምሳሌት ሆና ዘመናትን የተሻገረችው በፅኑ የሀገር ፍቅር፣ በተባበረ የሕዝብ ክንድ እና በጠንካራ መከላከያ ሠራዊቷ መስዋዕትነት ነው።
በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የሀገርን ሕልውና ለመናድ እና የሕዝብን ሰላም ለማደፍረስ የመጡ የውጭ እና የውስጥ ስጋቶችን በመመከት ረገድ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በግንባር ቀደምትነት የተሰለፈ ጽኑ መከታ ሆኖ ዘልቋል።
ዛሬ በደረስንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ሠራዊቱ የቆየውን የጀግንነትና የተጋድሎ ታሪክ ከዘመናዊ የመከላከያ ሥርዓት ግንባታ፣ ከሰው ኃይል ልማት፣ ከቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግና ከተለዋዋጭ የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ የደኅንነት ሁኔታዎች ጋር በማጣመር እንደ ብረት የጠነከረ፣ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ዋስትና የሆነ ተቋም ሆኖ በመገንባት ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ በድንገት የተገነባ ሳይሆን የታሪካዊ ተጋድሎ፣ ዘመናዊ የሪፎርም ሥራዎችና የዘመኑን ቴክኖሎጂ የመታጠቅ ውጤት ነው። የዓድዋ ድልና ተጋድሎ እንዲሁም የካራማራ የድል አድራጊነት መንፈስ ለዛሬው ሠራዊት የቁርጠኝነት እና የፅናት መሠረቶች ናቸው።
ይህ ታሪካዊ መሠረት ሠራዊቱ ለማንኛውም የሀገር ጥሪ ፈጣንና አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ አድርጎታል።
ዘመናዊ መከላከያ የሚገነባው በበቁና በሰለጠኑ አባላት ነው። የሠራዊቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎችና አካዳሚዎች የመኮንኖችንና የወታደሮችን የአመራር፣ የስትራቴጂክ አስተሳሰብና የውጊያ ብቃት በቀጣይነት በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
በዘመናዊው ውጊያ የመረጃ፣ የሳይበርና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎች ሚና ከፍተኛ ነው። ሠራዊቱ የድሮን ቴክኖሎጂዎችን፣ ዘመናዊ የመገናኛ ሥርዓቶችንና የሳይበር ደኅንነት መሰረተ ልማቶችን በመታጠቅ ስጋቶችን አስቀድሞ የመለየትና የመመከት አቅሙን አሳድጓል።
የዛሬው ወታደራዊ ስጋት ከመደበኛ ውጊያ ይልቅ መደበኛ ያልሆኑ የሃይብሪድና የሳይበር ጥቃቶችን ያካተተ ነው። ሠራዊቱ በእነዚህ ዘመናዊ ውጊያዎች ላይ ተለዋዋጭና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ስትራቴጂካዊ ዝግጁነት አለው።
የመከላከያ ሠራዊታችን ጥንካሬ በሚታጠቅበት የጦር መሣሪያና በአካላዊ ጉልበት ብቻ የሚለካ አይደለም፤ ይልቁንም በተቋማዊ እሴቶቹና በሞራል ጥንካሬው ላይ የተመሰረተ ነው።
ሠራዊቱ ለሕገ-መንግሥቱና ለሀገር ሕልውና ታማኝ የሆነ፣ በወታደራዊ ዲሲፕሊንና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የጦርነት ሕጎች መመሪያነት የሚንቀሳቀስ ፕሮፌሽናል ተቋም ነው።
የመከላከያ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ኅብረ-ቀለማዊ መግለጫ ነው። በየትኛውም የሀገራችን ክፍሎች በሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ከሕዝብ ጎን በመቆም፣ ሰላም በማስከበርና በመልሶ ግንባታ ላይ በመሳተፍ የሕዝቡን ሙሉ አመኔታ ያተረፈ ነው።
በከፍተኛ ስትራቴጂያዊ አመራርና በስልታዊ መዋቅር የተደራጀው ሠራዊት፣ የሀገርን ደኅንነት ከማስከበር አልፎ በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በኩል በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ለደኅንነት ዋስትና በመሆን ትልቅ ብሔራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን ሕልውና፣ የሕዝባችን ሰላምና የሉዓላዊነታችን ዋስትና የሆነ ጽኑ መከታ ነው። ያለፈውን የታሪክ ጀግንነት ከዘመኑ የቴክኖሎጂ አቅም፣ ከላቀ ዲሲፕሊን እና ከተቋማዊ ሪፎርም ጋር አዋህዶ በመጓዝ ሀገራችንን ከማንኛውም ስጋት የመጠበቅ ብቃቱን በተግባር አረጋግጧል።
ይህን የሕዝብ አለኝታና የሀገር ደኅንነት ጋሻ በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀትና በቁሳቁስ ይበልጥ በማጠናከር የሀገራችንን ሰላም፣ ልማትና ብሔራዊ ጥቅም በተስተካከለ መሠረት ላይ ማቆየት የሁላችንም ታሪካዊና ሀገራዊ ኃላፊነት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: